በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የፈተና አስተዳደርን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ያለመ ስልጠና እየተሰጠ ነዉ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ የፈተና ሥርዓትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የመረጃ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥና የፈተና አፈፃፀምን ለማሻሻል የሚያስችል የኦንላይን መዝጋቢዎች ስልጠና በቦንጋ ከተማ መስጠት ጀመረ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2017 እና 2018 የትምህርት ዘመናት የፈተና አፈፃፀም ግምገማና የስልጠና መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱት የቢሮው ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሜ ናቸው።

ዶክተር ደስታ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ የፈተና ሥርዓትን በቴክኖሎጂ መደገፍ የመረጃን ተዓማኒነት ከማረጋገጥ ባለፈ፣ መንግሥት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያጋጠመውን ስብራት ለመጠገን የወሰደው አይነተኛ እርምጃ ነው። በተለይም ከኩረጃ የፀዳ የፈተና አስተዳደርን ለማስፈን ክልሉ ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የኦንላይን ፈተናዎችን መስጠት መጀመሩን አስታውሰዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብና የፈተና ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል” ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህም በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የፈተናና የአይቲ (IT) ባለሙያዎች በቂ ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናው የተማሪዎችን የፈተና መረጃ በኦንላይን ስርዓት በትክክል ለመመዝገብ፣ የፈተና አስተዳደርን ለማዘመን እና የመረጃ ጥራትን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።

ይህንን የዲጂታል ሽግግር ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከቀለሜ ሜዳ ቴክኖሎጂስ ጋር በገባው ውል መሠረት፣ ስልጠናው በድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

በተያያዘም በመድረኩ ላይ የክልሉ የ2017 እና የ2018 የትምህርት ዘመናት የእስካሁን የፈተና አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። በዚህም የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ድክመቶችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማረም አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

በበረከት ኢዮብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *