ማሽቃሮ ባሮ ለሠላም ግንባታ ስራ የጎላ ፋይዳ አለው፦ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ (ማሽቃሮ ባሮ) በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅበው በአንድራቻ ወረዳ፣ ጌጫ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ማሽቃሮ ባሮ፥ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚጠያየቁበት እንዲሁም እውነተኛ ፍትህ የሚረጋገጥበት በመኾኑ ለሠላም ግንባታ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የለውጡ መንግሥት የህዝቦችን የጋራ ማንነት፣ ታሪክና ባህል በማልማትና በመጠበቅ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት የሚጫወቱትን ሚና እንዲያጠናክሩ ዕድል የፈጠረ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣

በዚህም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የማንነት መገለጫ የኾኑ ባህልና ታሪካቸውን በማልማትና በመጠበቅ እያጎለበቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከነዚህ የብሔረሰብ የማንነት መገለጫ በዓላት አንዱ ማሽቃሮ ባሮ መኾኑን የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሽ፥ በዓሉ የብሔረሰቡ የባህል መሪዎች ለአከባቢው ሠላም፤ መጪው ዘመን የደስታና የፍቅር እንዲሆን በጋራ የሚመረቁበት ነው ብለዋል።

በማሽቃሮ ባሮ የታየውን አንድነትና ማህበራዊ አብሮነት በማጠናከር ለአከባቢ እንዲሁም ለክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት እንዲሁም ለሠላም ለልማት ማዋል እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያስገነዘቡት።

የማሽቃሮ ባሮ ወጎችና ትውፊት በማልማት፤ ባህላዊና ታሪካዊ ዕሴቱን በመጠበቅ ለትውልድ በተገቢው ማስተላለፍ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ፣

በዚህም ህዴት የአከባቢው ምሁራንና በባህልና ታሪክ ጥበቃና ልማት ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሀላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው የዘንድሮው ማሽቃሮ ባሮ ኢትዮጵያዊያን በላብና በደማቸው የገነቡት ታላቁ የህዳሴ ግድቡ በተመረቀበት ማግስት በመኾኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ማሽቃሮ ባሮ የሸካቾ ብሔረሰብ አኩሪ ታሪክና ባህል አንዱ ማሳያ መኾኑን የጠቆሙት አቶ አበበ ይህ ድልብ የማህበረሰብ እውቀት ለዘመናዊ አስተዳደር መሠረት የጣለ እንደሆነም አስረድተዋል።

የማህበረሰቡ ቱባ ባህሎችን በማልማት የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ሚኒስትር አማካሪ አቶ ፀጋዬ ማማ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበዓሉ የሸካቾ የባህል ምክር ቤት ስራ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የባህላዊ ምክር ቤት አባላት ሹም ሽር ተደርጓል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *