



የሸካቾ ብሔረሰብ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በሸካቾ ባህል፣ቋንቋና ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበት ተጠናቋል።
የሸክ ኖኖ ቋንቋን ዘላቂ ዕድገትና ጥበቃ የማረጋገጡ ተግባር የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል።
የሀገር በቀል ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ መሠረት በመሆኑ ዕውቀቱን መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ተገልጿል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህር ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ የሸክ ኖኖ ቋንቋን ዘላቂ ዕድገትና ጥበቃ የማረጋገጡ ተግባር የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ይህ ጥረት የአካባቢውን ባህል፣ ታሪክ እና የማንነት መሠረት ከመጥፋት ለማዳን የሚደረግ ወሳኝ እንቅስቃሴ ነው ያሉት አቶ አልማው የሸካ ማህበረሰብ በቋንቋ ፣ በባህልና በሀገር በቀል እውቀት ላይ የበለፀገ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካል ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ለሸክ ኖኖ ቋንቋ ዘላቂ ዕድገትና ጥበቃ ማድረግ የአካባቢውን ባህልና የማንነት መሠረት ከመጠበቅ አንፃር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አቶ አልማው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሸካ ህዝብ የራሱ የሆነ የበለጸገ ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግና ልማድ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ የዳበረ ሀገር በቀል እውቀት እንዳለው የገለፁት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዝመራ አንደሞ ናቸው።
ሀገር በቀል እውቀትን ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ የሸካቾ ባህል፣ ቋንቋ እና ሀገር በቀል እውቀት ማዕከል መገንባትና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
የቋንቋውን ጠቀሜታ ዝቅ አድርጎ የማየት አሉታዊ አመለካከቶችን መለወጥ በቋንቋ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት መ/ር ብርሃኑ የግንዛቤና የአመለካከት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ መ/ርት አስቴር አለሙ በበኩላቸው በሀገራችን ከሚገኙ የቋንቋ ሀብቶች አንዱ የሆነው የሸክ ኖኖ ቋንቋ እንዲዳብርና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በቴክኖሎጂና በመገናኛ ብዙኃን መጠቀም
ቋንቋውን ከዛሬው ዓለም ጋር አብሮ እንዲራመድ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት መ/ሪት አስቴር ቋንቋውን በመዘገብና በማስተማር በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ክብርና አድናቆት መገንባት እንደሚገባ አንስተዋል።
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ከግለሰቡ ማንነት፣ ባህልና ቅርስ ጋር ተጣምሮ ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹበት፣ ታሪካቸውን የሚያውቁበትና ከማኅበረሰባቸው ጋር የሚተሳሰሩበት ዋናው መንገድ መሆኑን አመላክተዋል።
የሀገር በቀል ዕውቀት በማኅበረሰብ አባላት መካከል ያለውን ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያጠናክር የገለፁት የሸካ ምሁራን ማህበር ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ወርቅአፈራው አመነሸዋ ለዘላቂ ልማት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለባህል ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የሀገር በቀል ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ መሠረት በመሆኑ ዕውቀቱን መጠበቅ የባህል ሀብትንና የማኅበረሰቡን ማንነት መገለጫዎችን ይጠብቃል ሲሉም ገልፀዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ይከታተላሉን 👇
📌በፌስቡክ https://www.facebook.com/sowestcommunication/
📌በድረገጽ www.southwestcomunications.gov.et
📌በኢንስታግራም https://instagram.com/southwest_communications
📌በትዊተር twitter.com/sweprs
📌በቲክቶክ https://www.tiktok.com/@southwest.communi
📌በቴሌግራም https://t.me/Debubmierab
📌በዩቲዩብ youtube.com/@southwestgovcommunication
📌በዋትስአፕ
https://whatsapp.com/channel/0029VbAiSCpGE56ue7VyJJ3x
📌በሊንክደን
https://www.linkedin.com/company/southwest-communications/
