





በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የተዘጋጀው የ2017 በጀት ዓመት የ10 ወራት የአፈጻጸም ግምገማ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በተዘጋጀው የምክክር መድረክ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ውይይት በማድረግ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የእስካሁን የገቢ አሰባሰብ በሚፈለገው መጠን አለመከናወኑን ተናግረዋል ።
ገቢ የሚሰበሰብባቸውን የገቢ አማራጮች አሟጦ ከመጠቀም አንጻር በአመራሩና ባለሙያዎች ዘንድ በቁርጠኝነት ያለመምራት እንደ ችግር አንስተዋል ።
በግብር ከፋዮች ዘንድ ገቢን አሳንሶ የማሳወቅ፣ ዜሮ ሪፖርት ማቅረብና የደረጃ ሽግግር ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን የሚጠበቀውን ገቢ ለማሳካት አለመቻሉን እንደችግር አቅርበዋል ።
የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ አለመሆኑን በማንሳት በቀሪ ወራት አቅምን አሟጦ ገቢን ለመሰብሰብ ቁርጠኛ ሆነው ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል ።
በየደረጃው የሚሰበሰበውን ገቢ በተገቢው የመሰብሰብና ጥቅም ላይ ለማዋል የተዘጋጀው ደንብ ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀምና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተሳታፊዎች ተናግረዋል ።
ደረሰኞችን ለደንበኞች ቆርጦ የመስጠት ዝንባሌ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም በተፈለገው ልክ የታክስና ቲኦቲ ገቢ አሰባሰብ መሠረታዊ ችግር በመሆኑ ይህንንም ልዩ ኦፕሬሽን በመስራት አፈጻጸሙን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል ።
የውይይት መድረኩን የመሩት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገቢን በህግ ማዕቀፍ መሰብሰብና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር የገቢ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ በየወቅቱ በመገምገም ችግሮችን በመለየት ለገቢ ስራ ውጤታማነት በቁርጠኝነት መምራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በየአካባቢው የሚስተዋለውን የገቢ ስወራና ማጭበርበር ለመከታተልም የህግ ተፈጻሚነትን እያረጋገጡ መሄድ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የመሬት መጠቀሚያና ማዘጋጃቤታዊ ገቢ በዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸውን በመለየትና በማረም በቀሪ ወራቶች የሚጠበቀውን ገቢ ማሳካት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።
የሚሰበሰበውን ገቢ በተገቢው ለመምራትና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማስቻል የተዘጋጀው ደንብ በተገቢው ስራ ላይ እንዲውልም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሕይወት አሰግድ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አስተያየት ገቢን በዘልማድ ከመምራት አስተሳሰብ በመውጣት በዕውቀትና በቴክኖሎጂ መሠረት በማድረግ መፈጸም ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ለመሰብሰብ የተቀመጠውን የገቢ ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ ግብር ከፋዩ ዘንድ ቀረብ ብሎ በመደማመጥና ችግሮችን ለይቶ መፍታት ይገባል ብለዋል።
የገቢ አሰባሰብ ሂደት በአንዳንድ አካባቢዎች ፍትሐዊ ያልሆነ አካሄድን የሚከተል በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባውም ወ/ሮ ሕይወት ገልጸዋል።
በታጠቅ አበበ
