የተፈጥሮ ሀብትን ከጉዳት ለመጠበቅና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተገለጸ።

አቶ ደምሴ ደንቦ
Spread the love

ሪፖርታዥ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ሥጋት እየሆኑ ከመጡ ተግዳሮቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት እና የአካባቢ ብክለትና ብክነት ይጠቀሳል።
በኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና የአካባቢ ብክለትን በመግታት ለሰው ልጆች ፁዱ አካባቢና ምቹ የአኗኗር ሁኔታን ለመፍጠር መንግሥት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከእነዚህም ውስጥ የአረንጓዴ አሻራና፣ ብክለት ይብቃ፥ ውበት ይንቃ ፣ ጽዱ ኢት/ያ መርሃ ግብር እና የወንዝ ዳርቻ ልማትንና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዎችን ማንሳት ይቻላል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በክልል የደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዩች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የክልሉን አልፎም ሀገሪቱን ከአየር ንብረት ለውጥና ከአካባቢ ብክለት ችግር ለመታደግ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት በቢሮዉ ምክትል ኃላፊና የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለዉጥ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ደምሴ ደንቦ ናቸዉ፡፡
የክልሉ መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ብክለት እያሳደረ ያለውን ክልላዊና ሀገራዊ ተጽእኖ ለመቅረፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት በየአካባቢዉ በዘርፉ ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ የተለያዩ ንቅናቄዎችን በመፍጠርና ውጤታማ እንዲሆን ሕዝብን በባለቤትነት ያሳተፈ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዉ በክልሉ ማዕድን በሚመረትባቸው አካባቢዎች ከአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ደህንነት ስራዎች፣ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት ተደርጎ ከመግባባት መደረሱንም ገልጸዋል፡፡
እንደሳቸዉ ገለጻ፤በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከጉዳት ለመጠበቅና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ፣ አምራቾች፣ በየደረጃው ያለው ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት፣ ሁሉም አካላት በእኔነት ስሜት እንዲጠብቃቸው የሚያስችል ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ከብክለት ፅዱ ኢትዮጵያ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ክልልን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ ንቅናቄ ለማሳካት የተቀመጡ ግቦችን ፤ የህዝብ ንቅናቄ፣ የአካባቢ ህግ ማስከበር ስራን የማረጋገጥ ፣ትምህርትና ግንዛቤ በመፍጠር የአካባቢ ጥበቃ ሰራዎችን አጠናክሮ የመስራት እንዲሁም አካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ ፈርጀ ብዙ ሥራ እየተሰራ ነው።
የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የአገር ግንባታ ጉዳይ መሆኑንና በተለይም በክቡር ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መሪነት የአረንጓዴ አሻራ እንደ ሀገር ምሳሌ መሆን ያቻለ በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ መ/ቤት በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የተያዙትን የአገር ግንባታ ስራ በጋራ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መሥራት በሚያስችል ወቅት ላይ እንገኛለን በማለትም ገልጸዋል።
በክልሉ በማዕድን አምራችነት ዘርፍ ማለትም የወርቅ ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የግራናይት እና ላይም ስቶን ማዕድን አምራችነት ፍቃድ ወስደው እየሰሩ ያሉ አካላት ከአካባቢ ጥበቃና ማህበረሰብ ደህንነት ጥበቃ አንጻር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በሚመለከት የማዕድን ማምረቻ አካባቢዎች ላይ በጋራ ውይይቶችን በማካሄድ እየደረሱ ያሉ ተፅዕኖዎች ማቅለያ መንገዶች አተገባር አንጻር መግባባት መፍጠር መቻሉንም አቶ ደምሴ ደንቦ አስረድተዋል፡፡
ለሚያጋጥሙ የሚችሉና እያጋጠሙ ያሉ መሠረታዊ የአካባቢ ጥበቃና ማህበረሰብ ተፅዕኖዎችን ለመግታት የማቅለያ ስትራቴጂዎችን በማሰቀመጥና የተገመገሙ ተፅዕኖዎች ላይ ግብረ-መልስ በመስጠት ቀጣይ የአካባቢ ጥበቃ ህጎች ተግባራዊ ሆነው የአካባቢ መልሶ ማልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት በመፍጠር በየደረጃው የእርምት እርማጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ ተጠያቂነት በማስፈን ለዜጎች ዘላቂ ንፁህና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር ነው::
የክልሉ መንግስት የአካባቢ ደህንነትን መጠበቅ፣ ማስጠበቅና የተጎዱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙ የማድረግ ኃላፊነት እንደለበት አዉስተዉ በክልሉ ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ ተካሂዶ በአከባቢው እና በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልላችን በስፋት ማዕድን በሚመረትባቸው አካባቢዎች ለአብነትም በምዕራብ ኦሞ ወርቅ እና በዳውሮ ዞንና ኮንታ ዞን የድንጋይ ከሰል በሚመረትባቸው አካባቢዎች ከአካባቢ ጥበቃና ብክለት ቁጥጥርና ማህበረሰብ ደህንነት ጥበቃ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከወርቅ ማዕድን አምራች አንጻር በጥንካሬ የተገመገሙ ሥራዎች በወርቅ ማዕድን ማምረት የተሰማሩ ማህበራት መረጃ በተገቢዉ መንገድ ተደራጅቶ መቀመጡ፣የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ያላቸዉንና የሌላቸዉን ማህበራት መረጃ መያዙ፣የወርቅ ማዕድን የተቆፈረበት ቦታ መልሶ እንዲለማ በጀት ከመያዝ አንፃር የተወሰኑት ማህበራት ላይ መልሶ የማልማት ሥራ መጀመሩ፣ በየደረጃው በሥራ ሂደት ላይ በሚፈጠረዉ ከፍተኛ ክፍተት ከአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ በተወሰኑ ማህበራት ላይ ጥብቅ ክትትል መደረጉ እና አንዳንድ የወርቅ ማዕድን አምራች ማህበር ማዕድን የተቆፈረበትን ቦታ አፈር በመመለስ የተለያዩ ችግኞችንና ፍራፍሬዎች በመትከል አረንጓዴ ማድረግ የመልሶ ማልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆናቸው፡፡
በአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ደህንነት ልማት ሥራዎች ላይ የሲቪል ማህበራት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎችና ሃላፊነቶችን በአግባቡ መወጣት በተፈጥሮ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንደሚቻል አመላክተዋል።
በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የግራናይት እና ላይም ስቶን ማዕድን አምራችነት ዘርፍ ላይ ፍቃድ ወስደው እየሰሩ ያሉ ባለሀብቶች ከአካባቢና ማህበረሰብ ደህንነት ጥበቃ አንጻር በገቡት ውልና ህግ አግባብ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ በመጠቀም ዘላወቂና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ማምጣት ላይ የተሻለ ትኩረት በመስጠት ያለ በቂ ጥናት የሚካሄድ የማዕድን ቁፋሮ መስፋፋትና ኢንዱስትሪዎች ልማት በአካባቢና በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጎንዮሽ ጉዳቶችን ስለምያመጣ በጥንቃቄ በመስራት ጠንካራና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ አካባቢን እንፍጠር በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *