የእንስሳት ሀብት በተገቢው በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ በካፋ ዞን ሳይለም ወረዳ የተገነባውን የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል መርቀው ከፍተዋል።

በያዶታ ከተማ የተገነባው የቁም እንስሳት የግብይት ማዕከል በአከባቢው ያለውን የእንስሳት ሀብት በተገቢው ለመጠቀም የሚያግዝ መኾኑን ነው ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት የገለጹት።

የማዕከሉ መገንባት በአከባቢው ያለውን እምቅ የእንስሳት ሀብት ዘመናዊ ግብይት በማሳለጥ አርሶአደሩ ከቁም እንስሳት እርባታ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ በበኩላቸው፤ ዘመናዊ የግብይት ማዕከሉ የንግድ ስርዓቱን ለሁሉም ተዋናይ ክፍት በማድረግ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት የሚጨምር እንደኾነ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን ያመሰገኑት አቶ ታሪኩ፥ የግብይት ማዕከሉ መገንባት የክልሉ መንግሥት የንግድ ስነ-ምህዳር እስከታች ለማዘመን የጀመረው ስትራቴጂካዊ ጉዞ አካል ነው ብለዋል።

በምርቃት መርሐ-ግብሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *