በቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ምክር ቤት ከተማና መሠረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አሰገደች ወልደየስ በመድረኩ እንደገለጹት አስፈጻሚ ተቋማት የሚያከናውትን ተግባራት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ክፍተቶች ሲኖሩ የህዝብ አስተያየት መውሰድ የምክር ቤቱ አባላት ስነምግባርና ደንብ መካከል አንዱ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በአስፈጻሚ ተቋማት ለተሰሩ ጠንካራ ተግባራት እውቅና መስጠት ችግሮችን እየቀረፉ መሄድ የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮች መሳኝ ናቸው ብለዋል።

በዚሁ መድረክ በቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ላይ የሚስተዋሉ ችግር እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት በተለይም በመናኸሪያና ከታርፍ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት እንዲቻል የጋራ ውይይት እንደሚደረግም ሰብሳብዋ በንግግራቸው ጠቁመዋል።

የአስፈጻሚ አካላት ስርዓት በማጎልበት ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን እየፈቱ ለመሄድና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከህዝቦች ጋር የጋራ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም የገለጹት የካፋ ዞን ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ግርማ ደፋር ናቸው።

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ከተማና መሠረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኤነርጅ ቢሮ፤የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ከቦንጋ ከተማ ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በመድረኩ የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ እንዲሁም የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የስራ አፈጻጸም ረፖርት እየቀረበ ይገኛል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *