


በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በ74ኛው የአፍርካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ እየተሳተፈ ነው።
የአፍርካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት መድረክ ዛሬ ኮንጎ ሪፐብሊክ በብራዛቪል መካሄድ ጀምሯል።
እስከ ነሀሴ 25/2016 ዓ.ም በሚቆየው መድረክ በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራዉ የኢትዮጵያ ልዑክም በመድረኩ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ዛሬ በብራዛቪል ከተማ በይፋ በተጀመረው 74ኛው የአፍርካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት መድረክ የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ኒጌሶ መገኘታቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በመድረኩ ክልላዊ፣ አህጉራዊ፣ የማህበረሰብ ጤና አሁናዊና ቀጣይ ስትራቴጅክ ጉዳዮች ከዓለማችን ማህበረሰብ ጤና ጋር ያለው አጠቃላይ ሁኔታዎች ቀርበው ምክክርና ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተጠቅሷል።
ላለፉት 10 አመታት የአፍሪካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆነዉ ያገለገሉት ዶክተር ማቲሽዲሶ ሞኤቲን የሚተካ አመራርም በመድረኩ እንደሚመረጥ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
