

መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ሲያጠና ቆይቶ በተገበራቸው የኢኮኖሚ መሻሻያዎች አሁን ላይ ኢኮኖሚያችን በማንሠራራት ላይ ይገኛል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንት ታዬ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛው የሥራ ዘመን የ2018 የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር እያደረጉ ይገኛሉ።
በንግግራቸውም፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት በመዋቅራዊ ተግዳሮቶች ተጽዕኖ ሥር ወድቆ በከፍተኛ ዕዳ ጫና ውስጥ ይገኝ ነበር ብለዋል።
ከለውጡ መንግሥት በፊት ይመዘገብ የነበረው ዕድገትም በዘላቂ የፋይናንስ መሠረት ያልተዋቀረ፤ ሀገርን ለከፍተኛ ዕዳ የዳረገ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን የፈጠረ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥት እነዚህን የኢኮኖሚ መዛባቶች የሚያርሙ እና ወደ ብልጽግና ጎዳና የሚያደርሱ ፈጣን እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም የመንግሥት ገቢ፣ የወጪ ንግድ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
