
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የፌዴራል መንግስቱን ዓመታዊ ዕቅድ በዝርዝር አቅርበዋል።
በንግግርቸውም መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት በሁሉም ዘርፍ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።
በተለይም አሳታፊና አካታች የኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ በየዘርፉ አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ተግባራዊ መደረጉን አብራርተዋል።
የኢንዱስትሪ ማነቆዎቸን ለመፍታት ፈጣንና ጥራት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ማረጋገጥ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዘርፉ ለዜጎቸ የስራ እድል እንዲፈጥርና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዲያጎላ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማስቻል፣ ምርት ማሳደግ፣ ገበያ ማፈላለግና የቴከኖሎጂ ድጋፎች በስፋት እንዲቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለዘርፉ እድገት ወሳኝ የሆነ የሰለጠነ የሰው ሃይልን ጨምሮ ከፍተኛ ካፒታል ለሚጠይቁ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት እንደሚሰጥም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ለማጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጉልህ ሚና እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል።
መንግስት ካለፈው አመት የተሻገሩ ስራዎቸን ጨምሮ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ ተግባራትን በ2018 ዓ.ም አጠናከሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
መንግስት የዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማስፋት በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ የስራ እድሎችን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
