



ተስማሚ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ የምርምር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የግብርና የምርምር ኢንስቲትዩት የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በ1965 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ አካባቢ ያለውን የቅመማ ቅመም ምርት እንዲያስተባብር እንደ ሀገር የተቋቋመ የምርምር ተቋም መሆኑን የምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደረጀ ቱሉ ገልፀዋል፡፡
ምርምር ማዕከሉ በተለያዩ የምርምር መስኮች በተለይም በእፅዋት ጥበቃና ምርምር፣ በሰብል፣በእንሰት፣ አፈርና ውሃ አያያዝ ፣ መነሻ ቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ፣ ግብርና ኤክስቴንሽንና ኮሙኒኬሽን እንዲሁም በግብርና ኢኮኖምክስ ዘርፎች በዋናነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በግብርና ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ምርምሮችን በማካሄድ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማዕከሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ደረጀ ገልፀዋል።
በማዕከሉ በርካታ የተሻሻሉና ምርምር የተደረጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ በምርምር የተደገፉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን የፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ እና ሙዝ በማዳቀልና በማውጣት ወደ አርሶ አደሩ እያስፋፋ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የተጠቃሚውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ተስማሚ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ የምርምር ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል ፡፡
ከቅመማ ቅመም ምርት ባሻገር ለቡናና ለሌሎች ለሆርቲ ካልቸር ምርቶችም ምቹ ስነምህዳር ያለው አካባቢው በመሆኑ የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል እንደሀገር ከተቋቋመበት የቅመማቅመም ምርትን ከማስተባበር ባሸገር የአከባቢውን እምቅ አቅም መሠረት ያደረገ በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ስራ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ነው ዶክተር ደረጀ ያነሱት፡፡
የምርምር ማዕከሉ ለደቡብ ምዕራብ ብቸኛው የግብርና ምርምር ማዕከል በመሆኑና አርሶና አርብቶ አደር ማህበረሰብ የሚኖርበት ክልል በመሆኑ የምርምር ማዕከሉ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ በርካታ የምርምር ውጤቶችን በቅመማቅመም፣ በሰብልና በእንስሳት ዘርፍ በማውጣት እያስፋፋ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በእንስሳት ዘርፍም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን ማውጣት የተቻለ ሲሆን የሸኮ ከብት ዝሪያ ለክልሉ ብቻኛና በሽታን የሚቋቋም ዝርያ በመሆኑ ተጨማሪ የምርምር ስራዎችን በመስራት እያሳራጨን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
በርካታ የእንስሳት መኖ ዘር ዝሪያዎችን አውጥተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የእንቁላል፣ የወተትና የስጋ ምርታማነትን የሚጨምሩ የመኖ ዘር ማሻሻያ ምርምር ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
የአካባቢውን አቅም ያገናዘበ የማር ምርት ለማምረት እንዲያስችል 31 የእፅዋት አይነቶች ሊየታ ስራ መከናወኑን ገልጸው በቅመማ ቅመምና በቡና በየዓመቱ ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ችግኞችን ምርምር በማድረግ፣ በማፍላትና በማባዛት ለአርሶአደሩ እየተሰራጨ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ምርምር ማዕከሉ ከስራ ዕድል ፈጠራ አንፃር በቋሚና በጊዜያዊ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ስራ ዕድል መፍጠር የተቻለ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ደረጀ በዚህም ሴቶችና አቅማ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ መላው ማህበረሰብ በቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በየጊዜው የሚወጡ ዝሪያቸው የተሻሻሉ በርካታ የግብርና ምርምር ዉጤቶች እንዳሉና ከማዕከሉ የሚወጡ በቴክኖሎጂ የተሻሻሉ የምርምር ውጤቶችን ተጠቅመው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባቸዋል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
