




በምዕራብ ኦሞ ዞን ”ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተግባራዊ ሚና ፤ ከግጭትና ሞት አዙሪት ወደ ሁለንተናዊ ልማት በሚል መሪ ቃል የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ቀጣይ ትኩረት በሚያስፈልግበት ጉዳዮች ላይበጋራ በመመካከር ቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ላይ ዓላማ ያደረገ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ ባለፉት ዓመታት ከህዝቡ የሚነሱ የሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተለይም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሠላምና ፀጥታ የመደፍረስ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ካላቸው ፀጥታ መዋቅር እና ህዝቡን በማስተባበር ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ህዝቡ ለሳየው ትብብርና ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
በተሰራውም ሁለአቀፍ ስራ ሰላም ማስፈን በመቻሉ ሰፊ ክልላዊ እና ሀገራዊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም በርካታ እንቨስትመንት እንቅስቃሴና ፍስት እንዲጨምር ዕድል ፈጽሯልም ብለዋል።
በክልሉ በሁሉም ዞኖች በተሰሩ ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በምዕራብ አሞ ዞን ዘላቂነት ያለው ሰላምና ጸጥታ በማስፈን ህዝቡን በልማት ተጠቃሚ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዉበታል።
በዚህም ውስጣዊ እና ውጫዊ ግጭቶችና ዝርፊያዎች እንዲፈቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በየደረጃው ከሚመለከታቸው መዋቅሮችና አካላት ጋር በጋራ በተሰራው ውጤቶች እንደተመዘገቡም የገለጹት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ናቸው።
አቶ አንድነት አሸናፊ በክልላችን በተለይም በምዕራብ ኦሞ ዞን ባለፉት ጊዜያት ከተሰራው ስራ ልምድ በመውሰድ ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት የተረጋጋ ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ ህዝቡን ወደ ልማት ለማዞር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ የክልሉ የሁለቱም ምክር ቤቶች ዋና አፈ ጉባዔዎች ጨምሮ የክልሉ አስተባባሪ አካላት፣የፌደራልና የክልል ጸጥታ አካላት አመራሮች፣ የምዕራብ ኦሞ ዞንና የሁሉም ወረዳዎች አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።
በፍቅር ከበደ
