









የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ በፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ በየደረጃው ከሚገኙ የሚዲያ እና የፍትህ ተቋማት ጋር በቦንጋ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ዳንኤል፥ የፍትህ እና የሚዲያ ተቋማት ቅንጅት በማጠናከር በዘላቂነት የንቃተ ህግ እና የኅብረተሰብ ተሳትፎ ተግባራትን በማሳለጥ ለፍትህ ተደራሽነት መረጋገጥ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የፍትህ ትራንፎርሜሽን ዕቅዱ በሕዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለውን ጠንካራ የፍትህ ተቋም በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ መሠረት የሚጥል መኾኑን የገለጹት ኃላፊዎ፣
በዘርፉ ተቋማት የሚሰጠዉ አገልግሎት ከአድሎ፣ ከጉቦና ሙስና እንዱሁም ከሌሎች የሥነ-ምግባር ጉድለቶች በጸዳ መልኩ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ፍትህ እንዲያገኙ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የጎላ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ከዚህም አንጻር በክልሉ በሚፈጠሩ የህዝብ መድረኮች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች የሚያሳዩት በዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት፤ የአገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍና በሚፈለገው ደረጃ ሀብረተሰቡን የረካበት እንዳልሆነ መገንዘብ መቻሉን ነው ወ/ሮ ቤተልሔም የገለጹት።
በመሆኑም በፍትህ ዘርፍ ተቋማት ዉስጥ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የኅብረተሰቡን የፍትህ ፍላጎት ለማርካት በሶስት አመቱ የፍትህ ትራንፎርሜሽን እቅድ መሠረት ተግባራትን በትኩረት እየከወንን እንገኛለን ያሉት ኃላፊዎ፣ የሚዲያ ተቋማት መረጃን ተደራሽ በማድረግ ተግባሩን የማሳለጥ ሀላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሚዲያ ፎረሙ ሕግን ለህብረተሰቡ በተገቢው ማስገንዘብ ሕዝብን መሠረት ያደረገ ምላሽ ለመስጠት በፍትህ እና በሚዲያ ተቋማት መካከል ሊኖር ስለሚገባው የቅንጅት ስራ መሠረት የሚጥል መኾኑን ኃላፊዎ ገልጸዋል።
የሚዲያ ተቋማት የሕግ የበላይነትን አስመልክተው ለመላው የክልሉ ሕዝብ ንቃተ ሕግን ለመፍጠርና መረጃውን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ሕግ አክባሪ፣ መብቱን የሚያውቅና ግዴታውን የሚወጣ የነቃ ማኀበረሰብ ለመፍጠር ሃላፊነት በተገቢው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ፣ የነጻ የህግ ድጋፍ አግልግሎት እና የባህላዊ ፍ/ቤቶችን በሚመለከት ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
