



በካፋ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አመቻችነት በዞኑ የሚገኙ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች የመረጃ ሥርዓት ከማዘመን አኳያ በሚታዩ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የጋራ ውይይትና ምክክር መድረክ አካሂዷል ፡፡
የካፋ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ታከለ ታምሩ በመክፈቻ ንግግራቸው የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተቋማት የመረጃ ሥርዓት የዘመነ፣ ችግር ፈቺና የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል ፡
የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተቋማት እርስ በርስ ተቀናጅቶና ተናቦ የግብርና ምርትና ምርታማት ውጤቶችን፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ ውጤታማነትንና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንድሁ በዞኑ ውስጥ ያሉ እምቅ ጸጋዎችንና ሀብቶችን ለማስተዋወቅ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው ብሏል አቶ ታከለ ታምሩ ፡፡
በህዝብ አቅምና ገንዘብ ብሎም በመንግስት ድጋፍ እየተሰሩ ያሉትን የመሠረተ ልማቶች፤ የሌማት ትሩፋቶች እንድሁም በቡድንና በግለሰብ ደረጃ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በወቅቱና ተጨባጭ መረጃዎችን በማደራጀት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መዘገብ እንደሚገባም አቶ ታከለ አመላክተዋል ፡፡
የህዝብ ለህዝብ ጠንካራ ትስስርና አንድነት እንደዚሁም የገበያ ትስስርና ህገወጥ የምርት ቁጥጥር ዙሪያ ሁሉም ሚዲያዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
የሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች በተለይ አፍራሽ ተልዕኮዎችን ሚዛናዊ ሆኖ በመመከት ፤ ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመላበስና የአሰራር ሥርዓት ተከትሎ የህብረተሰቡን አንድነት በማጠናከርና የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ሚዛናዊ ሆኖ መረጃዎችን ሊያስተላልፉ ይገባልም ብለዋል አቶ ታከለ፡፡
የካፋ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ እሸቱ ለምክክር የሚሆን መነሻ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት ቀጣይ በሁሉም የሚዲያ ተቋማት የተግባር አፈጻጸም በማዘመን ፈጣን፣ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊና ተጨባጭ መረጃዎችን በማደራጀት ለመዘገብ ራሳቸውን ልያዘጋጁ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል ፡፡
አቶ አዳሙ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት የሚዲያ ተቋማት አሁን ላይ ከላይ እስከታች የሚያሳዩት መነቃቃትና በውድድር መንፈስ የሚያከናውኑት የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተግባር አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተቋማት ከአሰራር ሥርዓት ጋር ተያይዞ ከሚስተዋሉ ጉድለቶች መካከል የመረጃ ጥራት ችግር፤ተናቦ የመሥራት ጉድለት፤በተቋማት ደረጃ ውጤታማና ችግር ፈቺ ውይይት ያለማድረግ እንደዚሁም የበጀትና ሎጅስቲክስ ችግሮች ተግዳሮት እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡
ቀጣይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ተቀናጅቶና ተናቦ መስራት፤ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮን አማጦ መጠቀም፤ የመረጃ ሥርዓት ማዘመንና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ማዋል፤ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር የቅሬታ ምንጮችን ለይቶ መስራት የሚሉትና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ ይገባል በማለት አጽንኦት ሰጥቷል ፡፡
የመድረኩ ተሣታፊዎች በበኩላቸው ሀሣብ አስተያየታቸውን በስፋት ሰጥቷል።ከነዚህም መካከል የሎጅስቲክስ ፣የበጀትና የተሽከርካሪ ችግሮች ለአብነት በተግዳሮትነት ተነስቷል።
በተጨማሪ የሚዲያዎችና ኮሚኒኬሽን ትስስር ማጠናከር፤ ተከታታይ የምክክርና የሥልጠና መድረኮችን ማመቻቸት፤ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ማስቻልና በዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ማረም የሚሉት በውይይት ወቅት ከተነሱት ሀሣቦች መካከል ይገኙበታል ፡፡
ከተሳታፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎችና እሰተያየቶች የካፋ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታከለ ታምሩና የካፋ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ እሸቱ በቂ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡
የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተቋማት ተቀናጅቶ በመስራት የመረጃ ሥርዓት በማዘመን የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ እንደሚሰሩና የምክክር መድረክ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸዉን የዘገበዉ የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።
