የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love

ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ ሥር አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የካፋ፣ የዳዉሮ፣ የቤንች ሸኮ እና የሸካ ዞኖችን አጠቃላይ ገጽታን የሚያሳዩ፤ የካፈቾ ብሔር ባህላዊ ዱሞ ስርዓት፣ የዳውሮ ብሔረሰብ ዱቡሻ ስርዓት፣ የኮንታ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ሂንግጫ እና የሸካቾ ብሔረሰብ ለቅሶ ስነ ስርዓት የቃኙ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ የሸኮ ብሔረሰብ የምስጋና እና ዘመን መለወጫ በዓል /ቲካሻ ቤንጊ/ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ!

የሸኮ ብሔረሰብ በርካታ ታሪካዊ እና ባህላዊ ዕሴቶች ካሏቸው ማሕበረሰብ አንዱ ሲሆን የተለያዩ ባህላዊ የአስተዳደር፣ የዳኝነት፣ የእርቅ፣ የሽምግልና፣ የሰርግ፣ የለቅሶ፣ የሥራ፣ የምስጋና፣ ወዘተ ሥርዓቶችን ሲለማመድ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የምስጋና በዓላቸው ቲካሻ ቤንጊ(Tikasha Bengi) ሲሆን ባህላዊ ይዘት ያለውና በማህበረሰቡ ዘንድ የሚወደድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡
ብሔረሰቡ እንደ ህዝብ የራሱ የሆነ እምነት፣ ባህል እና ፍልስፍና የነበረዉ እና ያንኑ መሰረት በማድረግ የራሱን የዘመን አቆጣጠር ይከተል ስለነበር “ቲካሻ ቤንጊ”ም የሚመጣው በዚህ ዑደት ውስጥ ነው።
የሸኮ ህዝብ የዘመን አቆጣጠር የእርሻ ወቅትን መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡ ልክ ሌሎች ህዝቦች የመሬት ዙረትን ወይም ሉናር ካላንድርን እንደሚጠቀሙት የሸኮ ህዝብ የሰብል ምርት ዙር (Crop Rotation) ካላንደር ይጠቀማል፡፡ በዚህም ህዝቡ በድሮ ጊዜ የቀይ ማሽላ ወይም ዶንቃን፣ በቆሎን እና ሌሎች የስራስር ምግቦችን አብዝቶ ስለሚያመርት ቆጠራዉ እነዚህን መሰረት ያደረገ ነበር፡፡
የወቅት አቀጣጠርን አለም አቀፍ የመስፈርት አዉጭ ድርጅት አንድን አመት በአራት ወቅት ማለትም በጋ፣ ጸደይ፣ ክረምት እና በልግ ብሎ ሲከፍል የሸኮ ህዝብ ግን አመቱን “ኢሪቤንጊ እና ቱሩ ቤንጊ”ብሎ በሁለት ይከፍላል።
የሸኮ ብሔረሰብ የወር አቆጣጠራቸዉም የጨረቃ ዑደትን መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡ ልክ ጨረቃ እንደ አዲስ ስትወጣ አንድ ተብሎ ይቆጠርና አድጋ ጨርሳ ከጠፋችበት እስከ ምትወጣበት ጊዜ ድረስ አንድ ወር ተብሎ ይያዛል፡፡ ቀጥሎ እንደ አዲስ ስትወጣ ሁለት ተብሎ ይቆጠራል፡፡ በዚህ መልክ የአመት አቆጣጠሩ ይቀጥላል፡፡
የሸኮ ህዝብ ወራትን በሚቆጥሩበት መንገድ የቀናት አቆጣጠርን ስም ሰጥተዉ አይቆጥሩም ነበር፡፡ ነገር ግን የገበያ ቀናትን መሰረት አድረገዉ አንድ የገቢያ ሳምንት፣ ሁለት የገቢያ ሳምንት እያሉ ይቆጥሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሴቶች የእርግዝና ቀናቸዉን ለመቁጠር የወር አበባቸዉ ከቀረበት ጊዜ ጀምሮ ሰላሳ የገመድ ቋጠሮ ይቋጥሩና እሱን እየፈቱ ሲጨርሱ አንድ ወር ይላሉ፡፡ ደግመዉ ሰላሳ ይቋጥሩና እሱን እንደዚሁ ፈተዉ ሲጨርሱ ሁለት ወር እያሉ በዚሁ ልክ እስከ ዘጠኝ ወር ይቆጥራሉ፡፡
ህዝቦቹ በዋናነት እንደ አዲስ አመት መጀመሪያ ወር የሚጠቀሙት የማሽላ(ዶንቃ) እና የከቺ/ካሳቫ ምግቦች በእርሻ ዝግጅት መረሰት ተዘርቶ እስኪ ደርሱ አምስት ወራትን ይጨርሳል፡፡ ከዚያም ደርቆ ታጭዶ እስኪገባ ሁለት ወራትን ይወስዳል፡፡ ዶንቃዉ ታጭዶ ከገባ በኋላ ማሳዉ የቀጣይ አዲስ እርሻ እስኪጀመር ለሁለት ወራት ምንም ሳይሰራበት ይቆያል፡፡ ከዚያ እንደገና እርሻ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ይህ እርሻ የሚጀመርበት ወቅት አሮጌዉ አመት አልቆ አዲስ አመት እንደመጣ ይቆጠራል፡፡
የሸኮ ህዝብ እንደ ዘመን መለወጫ/አዲስ ዓመት/ የሚቆጥረዉ ለሚያንጉ የሚያቀርበውን የምስጋና ቀናት ሲሆን ይህ ስርዓት የሚካሄደዉ ጥር,ወር አከባቢ ግራዋ ሲያብብ እና ማር ሲቆረጥ ነዉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት በቆሎ እና ሌሎች ስራስሮች ሲደርሱ በግለሰብ ደረጃ አመርቂ ምርት ያመረቱ ሰዎች የምስጋና ድግስ ይደግሳሉ፡፡ ይህ ድግስ ትከሻ ይባላል፡፡ የዘራሁት እህል ከአዉሬና ከተፈጥሮ አደጋዎች ተርፎ በበቂ ደርሶልኛልና ደግሼ አብልቼ አምላኬን ማመስገንና ምርቃት ማግኘት ፈልጋለዉ ብሎ ያዘጋጃል፡፡
የቲካሻ ቤንጊ በዓል የሚከበረው የማር ምርት እና ሌሎች እህሎች ከተሰበሰቡ በኋላ ያረስኩት እህል በንፋስ አልተጎዳም፣ በአውሬ አልተበላብኝም፣ ልጆቼ በህመም አልተሰቃዩም፣ ህዝባችን በወረርሽኝ አልሞቱብንም፣ ከብቶቻችን በበሽታና በአውሬ አልጠፉብንም፣ ምድራችን ክፉ ነገር አልገጠማትም፣ ፈጣሪ ዝናብን እና ፀሀይን በወቅት አልነፈገንም በሚል ከተሰበሰበው ምርት ቦርዴ በማዘጋጀት፣ ከተሰበሰበው ማር ቦኬ/የማር ጠጅ/፣ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት፣ ቤታችን ጥጋብ ነው ኑ የደስታችን ተካፋይ ሁኑ የሚል ጥሪ ለዘመድ ወዳጅ በማስተላለፍ በአንድነት እየበሉ አየጠጡ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ጊዜ ነው፡፡
በሌላ ጎኑ ለቀጣይ ዓመት በህዝባችን ላይ የሚመጣ ቸነፈር ፈጣሪ ይመልስልን፣ ልጆች በሰላም ወጥተው ይግቡ፣ የተወለዱት ይደጉ፣ የተዘራው እህል ፍሬ ያፍራ፣ የተተከለው ተክል ስር ይያዝ፣ ምደሪቱ ሰላም ትሁን፣ ደኑ አየሩ ሰማይ ምድሩ ፈጣሪ ይጠብቅልን ተብሎ የእህል ዘር በአባቶች የሚመረቅበት ወቅት ነው፡፡
በዓሉ ሰርቶ ለፍቶ ምርት የሰበሰበ ሰው ሲደግስ ያልሰራ ደግሶ ሌላውን መጋበዝ ስለማይችል ላለማፈር ከስራ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ ለቀጣይ እርሻ ህብረተሰቡ በፉክክር እንዲሰሩ ተመርቀው ወደ ስራ የሚገቡበት እና የስራ ባህልን የሚያሳደግ ታሪካዊ የሸኮ ብሔረሰብ በዓለ-ክዋኔ ነው፡፡
በዚህ ወቅት መልካም የሰሩትን በማወደስ ጥፋት የፈጸሙትን በማውገዝ በከተማይቱ አደባባይ ወይም በንጉስ በረንዳ ላይ የተለያዩ ጭፈራዎችን በመጨፈር በድምቀት የሚያከብሩበት በዓል ነው፡፡
የብሔረሰቡ ንጉስ ከሕዝቡ ጋር የሚተዋወቅበት (የሚገናኝበት)፣ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የምርት ውጤት ያመጡ አርሶ አደሮች የሚበረታቱበት፣ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡ ደግሞ የሚመከሩበትና ለቀጣይ ዓመት በርትተው እንዲሰሩ ምክረ ሀሳቦች ተለግሰውላቸው እና ዕቅድ አቅደው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚገደዱበት ታሪካዊ ፋይዳ ያለው ኹነትም ነው ቲካሻ ቤንጊ፡፡
በዓሉ በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች ይነገራል፣ ይቀሰቀሳል ንጉሱ በሕዝቡ ፊት ዘውድ ይጫንለታል፣ በሕዝቡ ይሸለማል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ የንጉስ ሹም ሽረት ይደረጋል አዳዲስ አዋጆች፣ ደንቦች ለሕዝቡ ይገለፃሉ፡፡
በርካታ የእጅ ጥበብ ስራ ምርቶች የሚሸጡበት ባህላዊ ፋይዳ ያለው ቲካሻ ቤንጊ አብሮ መብላትና መጠጣት፣መደሰት እንድሁም የመከባበር እሴቶች ይታይበታል፡፡
በብሔረሰቡ መካከል የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመተጋገዝ፣ ይቅርባይነትና የእርቅ ሰላም ዕሴት በመሆን ከማገልገሉም ባሻገር የአንድነትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

በዓሉ የሚከበረው በወርሃ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን የዚህ በዓል አከባበር ስርዓት በተዋረድ ሁሉም የሸኮ ማህበረሰብ ከቤት ጀምሮ እያከበረ መጥቶ በስተመጨረሻም በአደባባይ ከሌሎች ወዳጆች ጋር ተከብሮ የሚጠናቀቅ የምስጋና እና ዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡
በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *