




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ባዘጋጀው የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ መድረኩን ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፤ መንግሥት የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመንና ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በመሆኑም የታክስ ማስከፈያ ምጣኔው አሁን ካለው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ የክልሉን የገቢ ምንጭ ከማሳደግ ባለፈ በርካታ መሠረታዊ ለውጦችን ይዞ እንደሚመጣ ተመላክቷል። ከእነዚህም መካከልየታክስ መሠረቱን ማስፋት፦ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፦ ዲጂታላይዜሽን እና
ለኢንቨስትመንትና ለንግድ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ የታክስ ማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት ማካተቱ ተገልጿል።
አቶ ወንድሙ ኩርታ አክለውም፣ አዋጁ ወደ ተግባር ከመሸጋገሩ በፊት ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በጥልቀት መፈተሽ እንዳለበት አሳስበዋል። ለዚህም የሕግ ባለሙያዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቂ ግብዓት በማቅረብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
“ይህ ማሻሻያ የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም ከመገንባት ባለፈ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ ፋይዳ አለው ስሉም አቶ ወንድሙ ኩርታ ገልጸዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
