




የመምሪያው የ2018 ዓ/ም በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻፀም ግምገማ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ መንፈቅ 2 ቢሊዮን 572 ሚልዮን 546 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ይታወሳል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ ፥ ባለፉት 6 ወራት ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ2 ቢሊዮን 578 ሚልዮን 4 መቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1 ቢልዮን 168 ምልዮን ብልጫ ያለው ሲሆን ይህም 83 በመቶ ዕድገት የታየበት አፈጻጸም መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ውጤት ቢጣ፣ ሺሾ እንዴ እና ጊምቦ ወረዳዎች በዞኑ ካሉት መዋቅሮች ከፍተኛውን የአፈጻጸም ድርሻ ከሚይዙት ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።
የዞኑን የገቢ አቅም ለማሳደግ የአሰባሰብ ስርአቱን ማጠናከርና የግብር ከፋዮችን ደረጃ የማሻሻል ተግባር ትኩረት እንደሚያስፈልገውም ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዞኑ በደረጃ ከደረጃ “ሀ” እስከ “ሐ” አጠቃላይ 20 ሺህ 193 ነጋዴዎች ያሉ ሲሆን በተለይ ከቫት ተመዝጋቢዎች የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑም ተመላክቷል።
በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ህገ ወጦች መበራከታቸው ለዘርፉ ፈታኝ መሆኑን ገልጸው ይህንን ከመከላከል ረገድ የሚመለከታቸው ሁሉ መተባበር እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
በሌላ መልኩ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ከሚጠበቀው በታች ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደመላሽ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ዘርፉ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
መድረኩ በቀጣይ ተግባራት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ቦንጋ ኤፍኤም ዘግቧል።
