የሾኬላ ዋሻና ፏፏቴ – ድብቁ የቱሪዝም ሀብት

Spread the love

የሾከላ ዋሻና ፏፏቴ የሚገኘው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በኮንታ ዞን፣ አመያ ዙሪያ ወረዳ በኦፓ ላሼ ቀበሌ ውስጥ ነው።

የዋሻው አጠቃላይ ይዘት እና ስፋት በዞኑ ውስጥ ካሉት ሌሎች ዋሻዎች ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዝ እንደኾነም ነው የሚገለጸው።

ሾከላ የሚለውን የዋሻው ስያሜ የተገኘው፥ ከዋሻው አናት ላይ በግምት ከ50 ሜትር በላይ ርቀት ወደታች የሚወረወረው ሾኬላ በተባለው ፏፏቴ ስም እንደተሰየመም ከዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዋሻው ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከአንዱ ዋሻ ወደ ሌላኛው ዋሻ ለመድረስ 100 ሜትር ርቀት አለው፡፡ የመጀመሪያው ዋሻ ሦስት ትላልቅና ስድስት ትናንሽ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የዋሻው ስፋት በግምት 300 ካሬሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የመግቢያ በር ከፍታው ደግሞ ሦስት ሜትር ያህል ነው፡፡

የዋሻው ሁለተኛ ክፍል የመኖሪያ ቤት 2 ሣሎን እንደሚባለው ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ክፍሉ በግምት 15×20 ሜትር የሚያክል ስፋት ሲሆን ክፍሉ ከሌላው ክፍል ጋር ተጠርቦ የተሰራ በሚመስል የድንጋይ ግድግዳ የተከለለ ነው፡፡

የዋሻው ሦስተኛው ክፍል ሰፋ ያለ ሲሆን በውስጡ የተለያዬ ቅርጽ ያላቸው ድንጋዮች እንዲሁም ከዋሻው ጣሪያ ያለማቋረጥ በሚንጠባጠበው ውሃ ጠብታ ከሚመስል ፈሳሽ የተሰሩ ውበት ያላቸው ጌጣጌጦች የተሞላ ነው።

በዋሻው ቀኝ በኩል ከላይ ቁልቁል ከ50 ሜትር እየተመዝገዘገ የሚወርደው የሾኬላ ፏፏቴ ለዋሻው ልዩ ግርማ ሞገስን ያጎናፈ ሲሆን በዋሻው ግራ በኩል ስድስት ትናንሽ ክፍሎችም ይገኙበታል።

የኮንታ ዞን በርካታ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ያሉት ሲሆን ከስድስት ዓመታት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በዞኑ በነበራቸው ጉብኝት “ኮንታ ፈጣሪ ሳይሰስት የእጁን ጥበብ የገለጸበት አከባቢ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

የሾኬላ ዋሻና ፏፏቴ ከዞኑ አመያ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ድንቅ የተፈጠረው ውብት ሲኾን ከዋሻውና ፏፏቴ በተጨማሪ በዙሪያ ገባው የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች፣ ነፋሻ አየር እና የአከባቢው ልዩ መልዐካ-ምድራዊ አቀማመጥ አይንን የሚማርክ ነው።

የቱሪዝም ሀብቱን በተገቢው የማስተዋወቅ፣ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ ማጠናከር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ነው የሚለው መልዕክታችን ነው።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *