




በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና አንድነትን ለማጠናከር የሚሰራው ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች እና የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ በአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከል እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ ኢትዮጵያ በርካታ የከበረና የዳበረ ባሕላዊ የሰላም ሐብቶች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
እነዚህ ሐብቶች ግጭቶችን በመፍታትና ሰላምን በማጽናት ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ አሁንም ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ባለድርሻዎች በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ይህ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክም በጋራ ለመምከርና ለሚያጋጥሙ ችግሮች በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ እንደሚያግዝም ተጠቅሷል።
መድረኩ “ማህበራዊ ሐብቶቻችን ለኀብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
