




የጤና ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርም አተገባበር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በስልጠና መድረኩ ላይ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊስ ላይ ስልጠና የሰጡት የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም ነፃ፣ ገልለተኛና ብዝሃነት ላይ ያተኮረ ተቋማት በመገንባት የሀገረ መንግስት ግንባታን ማጽናት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ትክክለኛውን ሰራተኛ በትክክለኛ ቦታ ላይ ለማስቀመጥ የሰራተኞችና የስራ መደብ ምዘና እንደሚካሄድ ገልፀው ሚዘናው የሰራተኛውን ጥቅም ለማስከበርና የተገልጋዩን አርካታ በማሳደግ ምርታማነትን ይጨምራል ብለዋል።
ሚዘናው የዝግጅት ምዕራፍ የትግበራና የማጽናት ደረጃዎችን እንደሚያልፍ የገለጹት አቶ ሳምሶን ሚዘናው ሰራተኛውን ከስራ ለማፈናቀል ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቄና መሰረተቢስ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በክልሉ በተለዩት አራት ተቋማት ማለትም የክልሉ ጤና፤ ሥራና ክህሎት፣ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት እና የፋይናንስ ቢሮዎች ላይ ሪፎርሙ ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ ተቋማትና ሰራተኞች አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባቸዋል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በሪፎርሙ ከተቋም እስከ ሰው ድረስ ሁሉ አቀፍ ለውጥ ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ ለሰራተኛውና ለተገልጋዩ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል።
በንጉሴ ወልደየስ
