የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

Spread the love

“ባህላዊ ስፖርቶቻችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን ” በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ ውድድር በኮንታ ዞን እየተካሄደ ነው።

በባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል ተሳትፎ ያደረጉ አካላት በሰጡት አስተያየት ውድድሩ አንዱ ከሌላው ልምድ የተካፈለበት መሆኑን ተናግረዋል ።

ወ/ሮ ገሊላ ሀ/ማሪያም ከካፋ ዞን በውድድሩ የተሳተፉ ሲሆን ባህላዊ ስፖርቶችና ፌስቲቫል ህብረብሔራዊነት ይበልጥ እንዲዳብር አስቻይ ናቸው ብለዋል።

የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል ከውድድር ባለፈም ልምድ የሚቀሰምበት ያልተነኩ ባህሎች ይበልጥ እንዲለሙ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ወ/ሮ ገሊላ ተናግረዋል ።

የኮንታ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ደምሴ በሰጡት አስተያየት የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል የአንድን አካባቢ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል ።

አሁን ላይ ህግ ያላቸው 13 የሚሆኑ ባህላዊ ጨዋታዎች ብቻ መኖራቸውን በመግለጽ እንደ ሀገር ከ200 በላይ መልማት የሚችሉ ዕምቅ ባህሎች ወደ አደባባይ እንዲወጡ ይህ ውድድር ማሳያም ነው ብለዋል።

የሸካ ዞን ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ተወካይ አቶ ብርሃኑ አያሾ በሰጡት አስተያየትም የውድድሮች መካሄድ የርስ በርስ ግንኙነቶችን ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛሉ ብለዋሉ ።

የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል ውድድሮች ሰላምን የበለጠ ለማጽናት ወደር የላቸውም ብለዋል።

የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በየነ ቴቃ በበኩላቸው የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል በክልሉ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ቱባ ባህሎችን በአደባባይ የማስተዋወቅ ስራ መሻሻሎች የታዩበት ነው ብለዋል።

የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል መካሄድ የርስ በርስ ግንኙትን የሚያጠናክር፣አንዱ ከሌላው ልምድ የሚቀስምበት፣ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያንሰራሩበት ትልቅ ሁነት ነው ሲሉም ተናግረዋል ።

የክልሉ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አፈወርቅ ዳና ነባር ባህላዊ ስፖርቶች ወደ አደባባይ ወጥቶ ደምቀው እንዲታዩ ለማስቻል ውድድሮቹ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።

ውድድሮች በተለያየ ጊዜ በተለያየ የክልሉ አካባቢዎች መካሄዳቸው ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የገቢ መዳበር አስዋጽኦው የላቀ መሆኑንም አቶ አፈወርቅ ተናግረዋል ።

አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ ለምተው ጥቅም ላይ ከዋሉት ባሻገር ሌሎች ባህሎች ላይ ትኩረት በመስጠት ይበልጥ እንዲለሙ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባልም ሲሉ ጠይቀዋል።

በአራተኛው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል የተለያዩ የስፖርት አይነቶች ውድድር እየተደረገባቸው ይገኛል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *