ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ለሸኮ ብሔር ቲካሻ ቤንጊ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ቲካሽ ቤንጊ በሸኮ ብሔር የአዲስ ዘመን ብስራት ፣የምስጋናና አብሮነት የሚገለጽበት በዓል መሆኑን በመልዕክታቸው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ታሪክ፣ባህልና እሴቶች ባለቤት መሆኗን በመጥቀስ ከነዚህ ደማቅ ማንነቶች አንዱ ቲካሽ ቤንጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

የሸኮ ብሔር ሠላም ወዳድ ፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን እሴትን በመላበስ ለዘመናት ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላምና በፍቅር የኖረ ህዝብና አከባቢ እንደሆነም ነው ያወሱት አቶ ወንድሙ የበዓሉ መከበር ይህንን የጋራ ዕሴት የሚያጎላ መሆኑንም ነው ጨምሮ የገለጹት።

ቲካሻ ቤንጊ የሸኮ ብሔር ከክረምቱ ፅልመት፣ ጎርፍና መብረቅ ፈጣሪ በሰላምና ጤና ጠብቆና አሻግሮ እዚህ ላደረሳቸው ፈጣሪ የምስጋና የሚያቀርቡበትና የአዝመራው እሸት (የበኩር ምርት) በታላላቅ አባቶች ምርቃት ተደርጎ የሚቀመስበት አኩሪ ባህል መሆኑንም ነው አቶ ወንድሙ ያወሱት።

አምና ለመጀመሪያ ጊዜ ቲካሻ ቤንጊን እጅግ ባማረ ፣ በደመቀና በተሳካ ሁኔታ መከበሩን ያነሱት ዋና አፈ ጉባኤ የዘንድሮ በዓል ከአምናው ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ህዝባዊ መሰረት በማጽናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍም መሠረት የተጣለበት ነው ብለዋል።

በዓሉ የፍቅር ፣ የአብሮነት ፣ የምስጋናና ወዳጅነታችንን የምናጠናክርበት በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለው ያሉት አቶ ወንድሙ ለመላው የሸኮ ብሔር ተወላጆችና ወዳጆች እንኳን ለቲካሻ ቤንጊ በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *