ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢንቨስትመንት ከባቢውን ምቹ ያደረጉ የማሻሻያ ተግባራት ተከናውነዋል

Spread the love

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢንቨስትመንት ከባቢውን መቀየር ያስቻሉ በርካታ ስኬታማ ማሻሻያዎች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዐቅም ለማሳደግ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተነድፎ ዓይነተ-ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሚያተኩርባቸው ዘርፎች አንዱ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ፍሰት በይበልጥ ማሳደግ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም የኢንቨስትመንት ምኅዳሩን ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

ከነዚህ መካከል የሕግ ማሻሻያ በማድረግ የኢንቨስትመንት ከባቢውን ተገማች እና ግልጽ ወደሆነ የኢንቨስትመንት ዐውድ ለመቀየር ያስቻሉ ከ120 በላይ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል።

ማሻሻዎቹን ተከትሎም ለበርካታ ዓመታት ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ ሴክተሮችን ክፍት በማድረግ እንዲሳተፉበት ተደርጓል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ጥረት ተሳክቶ አባልነቷ ሲረጋገጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን በይበልጥ እንደሚያሳድገው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በቅርቡ ወደ ተግባር የገባው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ማደግ የጎላ ሚና እንዳለው አመላክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *