






የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በታርጫ ከተማ እየመከረ ነው ።
በምክክር መድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባስተላለፉት መልዕክት በግማሽ ዓመቱ የተሻለ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል ።
በገቢ አሰባሰብ ሂደት ውስጥ የተገኘውን ጥንካሬ ማስቀጠልና በድክመት የታየውን በመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ለገቢ ውጤታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።
ገቢን መሰብሰብ የሚያስችል አቅም እያለ በአቅም ልክ መሰብሰብ ያልቻልንበትን ችግሮች በመለየትም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በትኩረት መሰብሰብ ይገባልም ብለዋል።
ክልላዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን ከሰው ንክኪ ውጭ በሆነ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ መደረግም አለበት ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎም የደረጃ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ግብር ከፋዮች በመለየት በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
በገቢ አሰባሰብ ሂደት ውስጥ የህግ የበላይነትን በማስፈን የፖለቲካ አመራሩ፣የፍትህ እና የፖሊስ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩም እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።
ክልላዊ የገቢ ዕቅድ 10.07 ቢሊዮን ብር ለማሳካት የተለያዩ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም ማሳካት ይገባናል ብለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ 60 ከመቶ በውስጥ ገቢ ለመሸፈን ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ግብርን በቴክኖሎጂ በመታገዝ የማዘመን ስራዎችን ዕውን ለማድረግም በ66 የታክስ ማዕከላት ሲሰራ መቆየቱንም ወ/ሮ ህይወት ተናግረዋል ።
በክልል ቢሮዎች የሚሰበሰበውን ገቢ የኢታክስ ስርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉን የገቢ ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ በአንዳንድ ተቋማት ልልነት የታየበት አሰራር መኖሩ በሚፈለገው ልክ ገቢን ለመሰብሰብ ተግዳሮት በመሆኑ ህግን በማስከበር የሚፈለገውን ገቢ ስኬታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል ።
ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የአፈጻጸም ሪፖርት በቢሮ የልማት ዕቅድ ዳይሮክቶሬት በሆኑ በአቶ ጂብሪል አባጊሳ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።
በታጠቅ አበበ
