




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን ሳይለም ወረዳ ተቺቢ ቀበሌ በ31 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ግንባታ እና 6 ኪሎሜትር በህዝብ ተሳትፎ የተሰራ የመንገድ ልማት ሥራ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ( ዶ/ር) ፕሮጀክቶቹን መርቀዉ በከፈቱበት ወቅት እንዳሉ፤ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ዝቅተኛውን የክልሉ የዉሃ ሽፋን እያሻሻሉ ይገኛሉ።
የሳይለም ወረዳ ህዝብ የረዥም ዘመን ጥያቄ የነበረው የተለያዩ የልማት ጥያቄዎችን የክልሉ ህዝብ ተቀብሎ በደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቆሙት።
ከእነዚህም ውስጥ የያዶታ ጤና ተቋም ግንባታ ማስፋፊያ፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል፣ ዘመናዊ የእንስሳት ግብይት ማዕከል እና ሌሎች የመንገድ ልማት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።
እንደክልል በማህበራዊ ልማት ሥራዎች በተለይም በገጠሩ አከባቢ የጤና፣ትምህርት እንዲሁም በሌሎች መሠረተ ልማት ሥራዎች እያከናወነ ያለው ተግባራት መንግስት እና ፓርቲው ለሰዉ ተኮር ሥራዎች የሰጠዉ ትልቁ ማሳያ ነው ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር በማከልም የወረዳ አስተዳደር እና ህብረተሰቡ በየጊዜው ከመንግሥት የሚወርዱ የገጠር ኮሪደር ልማትና ሌሎች እንሼቲቮችን ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የክልሉ ዉሃ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸዉ በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት 271 የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀከቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ ህብረተሰብ ክፍለ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶችም ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተሰሩ ሲሆኑ ይህም በክልሉ መንግስት፣ መንግስት ባልሆኑ የልማት ድርጅቶችና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሰሩ ናቸዉ።
ወደ 150 ሺህ የሚጠጋ የክልል ህዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ 25 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎች በግንባታ ሂደት መገኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
በካፋ ዞን ሳይለም ወረዳ ተቺቢ ቀበሌ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት 31 ሚሊዮን ብር ወጪ የወጣበት ነው ያሉት ኢንጂነር በየነ ይህም ከ3ሺህ በላይ ህዝብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
በወረዳዉ ከዚህ በተጨማሪ በፌደራል እና በክልሉ መንግስት ትብብር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 437 ክሎዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የሶላር ፕሮጀክት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።
የሶላር ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ለከተማው ነዋሪ ኃይል ከመስጠት ባሻገር ዉሃን ለመግፋት የሚወጣውን የነዳጅ ወጪ እንደሚቀንስ ኃላፊው ጠቅሰዋል።
ኢንጂነር በየነ በላቸው የውሃ ተቋማትን መገንባት ብቻውን ፋይዳ ስለማይኖረው ህብረተሰቡ የተገነባውን የዉሃ ተቋማት ማህበር በማቋቋም ብልሽቶች ሲገጥሙ እየጠገነ በእንክብካቤ እንዲይዝ አደራ ብለዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በዞኑ በክልሉ መንግስት እና በፓርቲው መሪነት መሠረተ ልማት፣ ጤና እና ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ልማት ሥራዎችን ማዕከል ተድርገዉ የሚከናወኑ ተግባራት የህዝቡን የዘመናት ጥያቄዎችን እየመለሱ ናቸዉ ብለዋል።
ወረዳዉ በሰብል፣ በቡና፣በማርና በእንስሳት ሀብት የሚታወቅ አከባቢ ነው ያሉት የሳይለም ወረዳ አስተዳደሪ አቶ አማኑኤል ኃይሌ በአከባቢው ያለውን ጸጋ ወደ ሀብት መቀየር እንዲቻል መንግሥት እያደረገ ያለው የልማት ሥራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ በየደረጃው ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በፍቅር ከበደ
