የጸረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ ተቋማዊ አደረጃጀትና አሠራር ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ዓለም አቀፍ የጸረ-ሙስና ቀን “ትወልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር!” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

በመድረኩ አጠቃላይ የተቋሙ ሠራተኞች እና አመራር በተገኙበት ለዕለቱ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እና በቀጣይ የጸረ ሙስና ትግሉን ውጤታማ የሚያደርጉ አስተያየቶች ተሰጥበታል፡፡

የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመንግሥት መረጃ ማዕከል አስተዳደር እና ዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር መስፍን ወዳጆ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ ሀገራችን የጀመረቻቸውን የሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በፅናት መታገል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሙስና የፀዳች እና ሁሉንም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በማቋቋምና ልዩ ልዩ አሰራሮችን በመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነ አንስተው ለዚህም ሁሉም ዜጋ በመከላከሉ ላይ ትግል በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጣ ይገበዋል ብለዋል፡፡

የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ስለ ሙስናና ብልሹ አሰራር አስከፊነት በቂ ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ በወጣቱ ትውልድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅም ዶክተር መስፍን ተናግረዋል፡፡

የቢሮው ስነምግባርና ፀረ-ሙስና መኮንን ተወካይ አቶ ታምራት ቆጭቶ የዕለቱን የመወያያ ሰነድ ለሠራተኞች ባቀረቡበት ወቅት፣ በመንግሥት አገልግሎት አሠጣጥ ላይ የሚታዩ ሙስናና ብልሹ አሠራር ለመከላከል በየደረጃው ሰፊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መቆየቱን ገልጿል፡፡

በሕዝብ አገልግሎት ውስጥ ያለውን የጥቅም ግጭቶችን በመቆጣጠር በሁሉም ውሳኔዎች ላይ ቅልጽነት ያለው እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ እና የተቋሙ ሠረተኞችም ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል ትግል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አንስቷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የቢሮው ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት ሙስናና ብልሹ አሠራር እጅግ በተጠና ውስብስብ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ተግባር መሆኑንና ይህንን በተደራጀ በመከላከል የጸረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ ተቋማዊ አደረጃጀትና አሠራር ማጠንከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ለዚህም በሙስና ትግል ንቁ ተሳታፊ ሆነው በመንቀሳቀስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ገልጸዋል።

በተከተል ወ/ሚካአል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *