የሠላምና የሀገረ-መንግስት ግንባታ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

Spread the love

ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የተዘረጉ የሠላም እና የሀገረ-መንግስት ግንባታ ስራዎች በተጠናከረ እና በተቀናጀ መልኩ ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለፀ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት “የሀገረ-መንግስት ግንባታ መሰረታዊያን፤ ሀገራዊ ማንነት፣ ሀገራዊ ጥቅሞች እና እሴቶች ለዘላቂ ሠላም” በሚል መሪ ቃል ለባለድርሻ አካላት በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ መሰለ ከበደ፣ የሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ እንዲፈጥን የሠላም ማረጋገጥ እና የሀገረ-መንግስት ግንባታ ስራዎች ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደቱን ለማቀላጠፍ ከየኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር በተለያዩ መዋቅሮች ወጥነት ያለው ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ይህም ሁሉም ዜጋ በሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያግዛል ብለዋል።

የሀገረ-መንግስት ግንባታን ከግጭት አፈታት ስትራቴጂ ጋር በማስተሳሰር የህዝቦች አንድነትና ትስስር ለማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ገዥ ትርክት እንዲጠናከር እና ነጠላ ትርክቶች ጠርዝ እንዲይዙ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በውይይትና በስልጠናዎች የሚቀርቡ ሀሳቦች ጎልተው እንዲወጡ እና የሀገረ-መንግስት ግንባታ አጀንዳ በሁሉም ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ሁሉ አቀፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ምክትል አፈ-ጉባኤው አንስተዋል።

ይህ ስልጠና በቀጣይም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንደሚወርድ ጠቅሰው ፣ በሁሉም ደረጃ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በቂ ትኩረት እንዲሰጡት ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት በሀገረ-መንግስት ግንባታ፣ በሀገራዊ ማንነት፣ በሀገራዊ ጥቅሞችና እሴቶች ላይ የሚያተኩር ሰነድ እየቀረበ ይገኛል።

በስልጠናው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያምን ጨምሮ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አፈ-ጉባኤዎች፣ የፀጥታ መምሪያ ሀላፊዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች ፤በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በበረከት ኢዮብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *