ባለፋት ስድስት ወራት በክልሉ ማኅበረሰብን በማሳተፍ መደበኛና የንቅናቄ አጀንዳዎችን በተሻለ መልኩ መፈጸም ተችሏል – እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የመንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ የተግባር አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ እየተገመገመ ነዉ።

ባለፋት ስድስት ወራት በክልሉ ማኅበረሰብን በማሳተፍ መደበኛና የንቅናቄ አጀንዳዎችን በተሻለ መልኩ መፈጸም መቻሉን ነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የገለጹት።

በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በማከናወን ወደ ተግባር መገባቱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተቋማትና በመዋቅር ደረጃ የተደረገው የአመራር ምዘና መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራር እስከ ታቸኛው መዋቅር በመውረድ ያደረጉት ድጋፍ ችግር ፈቺ እንደነበረ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይህንን የድጋፍ አግባብ በቀጣይም አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ ማኅበረሰብን በማሳተፍ በማኅበራዊ በልማትና በመሠረተ ልማት ግንባታ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሽ፥ ተግባሩ በቀጣይም መጠናከር አለበት ብለዋል።

የክልሉ የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ ትኩረት የተሰጠው የገቢ ዘርፍ መኾኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የገቢ መሠረት በማስፋትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የክልሉን የገቢ አቅም ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ የግብርና ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ መደበኛ ተግባራት ውጤታማ መኾናቸውን የገለጹት ዶ/ር ነጋሽ፥ የምርት ዘመኑ የክልሉ የግብዓት ዕዳ ወደ ዜሮ መውረዱን አስረድተዋል።

ምንም እንኳን በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሁሉም ዘርፍ አበረታች ዕድገት እየተመዘገበ የመጣ ቢኾንም፣ በመዋቅርና በተቋማት መካከል የሚስተዋለው የአፈጻጸም ልዩነት ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *