
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ረገድ አይነተኛ ሚና እንዳለው አቶ ወንዱ ታደሰ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የደንበኞች አገልግሎት የገቢ አሰባሰብና አወሳሰን ዘርፍ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
አቶ ወንዱ ታደሰ የደንበኞች አገልግሎት የገቢ አሰባሰብና አወሳሰን ዘርፍ የግብር ከፋዩን መረጃ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በማደራጀትና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዘመናዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በመገንባት የክልሉን መንግስት ወጪ በገቢ ለመሸፈን የተያዘውን ራዕይ በማሳካት የክልሉን ህዝቦች ያደሩ መሰረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ስር ተደራጅቶ ይህን ስራ ካሉት ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ ወንዱ በክልሉ ከሁሉ ቀድሞ አገልግሎቱ በገቢ ተቋም በኩል እንደጀመረ ገልፀዋል፡፡
በዚህም ለክልሉ ከፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በቁጥር ዘጠኝ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የሚደራጅበት መሳሪያ የተሰጠ ሲሆን አገልግሎቱ በስድስቱ ዞን ማዕከሎች፤ በቦንጋና ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በክልል ማዕከል ዜጎች እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት አስር ወራት 7,700 የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎት ማግኘታቸው ነው የተገለፀው፡፡
በዚህ ተግባር በስራ ላይ እያለ ብልሽት የገጠመውን የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ መረጃ የሚደራጅበት መሳሪያ በፍጥነት በማስተካከል እንዲሁም በሸካ ዞን ስራውን ለመስራት ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች ወደ ሌላ አካባቢ በስራ ምክንያት በመሄዳቸው የተፈጠረውን ችግር በቅርበት ደግፎ በመፍታት ስራውን ለማስቀጠል በቅንጅት ርብርብ መደረጉን አቶ ወንዱ ታደሰ መግለጻቸዉን የቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የላከልን መረጃ ያመለክታል።
