











የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም እየተገመገመ ነው።
የርዕሰ መስተዳድሩ የኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር ኢንጂነር ምትኩ በድሩ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቋማትን የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል ።
ሪፖርቱን ያቀረቡት አማካሪው በነዚህ ተቋማት ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ተጨባጭ እና ውጤታማ የሆኑ ተግባራት መከናወናቸውን በሪፖርቱ አመላክተዉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለይተዉ ለዉይይት አቅርበዋል።
በአፈጻጸም ሪፖርቱ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው የገመገሙ ሲሆን አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በግብርና ልማት ስራዎች ፣ በገቢ ልማት ስራዎች በኢንቨስትመንት ተደራሽነትና ሌሎች ተግባራት የሚበረታቱ ስራዎች መኖራቸውን ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በከተማም ሆነ በገጠር እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ሊሰሩባቸው እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በቀረበው አስተያየቶች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በሰጡት ማጠቃለያ በአንደኛው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ከዝግጅት ባለፈ ውጤት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል ።
በግብርናው ዘርፍ የወረዱ የንቅናቄ አጀንዳዎች በየዕለቱ በመከታተል ውጤታማ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
በከተማና በገጠር የመሬት አስተዳደር ስርዓቶችን በተገቢው መንገድ መምራት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።
የትላልቅ ከተሞችን ማስተር ፕላን ከከተሞች ዕድገት አኳያ ማደስ ይገባልም ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ገቢ በየዞኑ ያለውን ዕዳ ትኩረት በመስጠት ማስመለስ ይገባልም ብለዋል።
በክልሉ በታቀደው የገቢ አሰባሰብ ዕቅድ አፈጻጸሙ በሚፈለገው ልክ እንዲከናወን የገቢ አሰባበሰብ ስልትን በመፈተሽ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
በአንደኛው ሩብ ዓመት በየተቋማቱ የተገኘውን ውጤት በማስቀጠል በ2ኛው ሩብ ዓመት የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገብ ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በነዚህና ሌሎች በተነሱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማትና የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ሴክተር ዘርፍ የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ እንደሚገመገም ለማወቅ ተችሏል።
በታጠቅ አበበ
