ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

Spread the love

ኮሚሽኑ በክልሉ 34 ወረዳዎች የአደጋ ስጋት እንዳለባቸው አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ለማ መሰለ በክልሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በክልሉ 34 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 269 ቀበሌዎች የአደጋ ስጋት ቀጠናዎች ተብለው መለየታቸውን አንስተዋል።

ከሰሞኑ በካፋ ዞን ጨና ወረዳ ኮዳ ቀበሌ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ290 በላይ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

ከዝናብ መጨመር ጋር ተያይዞ መሰል ጉዳት እንዳይደርስ ማህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሰገንዝበዋል።

ጉዳቶችን ለመቀነስ በኮሚሽኑ የሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው ፤ አደጋው የደረሰበት ጨና ወረዳ ኮዳ ቀበሌ የምግብና የሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መኖሩን አስረድተዋል።

አደጋ የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በየደረጃው ያሉ አካላት መደገፍ እንዳለባቸው ዶክተር ለማ አሳስበዋል።

አሁን ወቅቱ ዝናብ የሚበረታበት በመሆኑ ፤ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል ደሬቴድ ቦንጋ ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *