ከጤና ዘርፍ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር የዉይይት መድረክ በሸካ ዞን እየተካሄደ ነዉ

Spread the love

“የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገራዊ ዕድገት ” በሚል መሪ ቃል ከጤና ተቋማት ባለሙያዎች ጋር ዞን አቀፍ የውይይት መድረክ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ እንደገለፁት መንግስት በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቱን ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።

መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ጤና ለማስጠበቅና በዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማረም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል ዋና አስተዳዳሪው።

አክሞ ማዳን እና መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ እየተተገበረ ይገኛሉ ያሉት አቶ አበበ እየተስተዋሉ ያሉ ጉድለቶችን ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባቦት በመፍጠር ለተገልጋዩ ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ገልፀዋል።

በጤናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ለተመዘገበው ስኬት የዘርፉ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበው አበርክቷቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ በበኩላቸው የጤናውን ዘርፍ ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል።

በዞኑ 228 የግልና የመንግስት የጤና ተቋማት መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍና የማህበራዊ ዘርፍ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።

በቀጣይም የጤና አገልግሎቱን ይበልጥ ለማጠናከርና የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ በሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ እየቀረበ ይገኛል።

እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ ላይ ለረዥም ዓመታት በጤናው ዘርፍ ያገለገሉ አንጋፋ የጤና ባለሙያዎች አቶ በፍቃዱ ነጋዎ እና አቶ ኡስማን ኢብራሂም ተሞክሯቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞን ጨምሮ ከሁሉም መዋቅር የተውጣጡ የጤና ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *