






የማጃንግ ብሔረሰብ የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም የብሔረሰቡ ተወላጆችና ወዳጆች በተገኙበት በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በፓናል ውይይት ተጀምሯል ።
የብሔረሰቡን ቀደምት እሴቶችን ለማነቃቃትና ለማልማት ያለመው የመጀመሪያውና ታሪካዊው የየቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም: ቱባ ባህሉ ይዘቱን ጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድና ለዓለም ለማስተዋወቅ መሠረት የሚጣልበት ታላቅ ቀን መሆኑ ተመላክተዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ የለውጡ መንግስት እውነተኛ ህብረብሔራዊ ፌደራሊዝምን የሚያፀና በመሆኑ የዞናኑ ነባር ብሔረሰቦች ላለፉት 3 ዓመታት የባህል ልማት ላይ አትኩሮ መስራቱን ገልጸዋል።
የማጃንግ ብሔረሰብ በዞናችን ውስጥ ከሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን የራሱ የሆነ ቋንቋና ባህል ኖሮት ከሌሎች ወንድም ብሔረሰቦች ጋር ተዋዶና ተከባብረው እንዲሁም እንግዳ ወደ ቀዬው ሲገባ በሞቀ አቀባበል በማስተናገድ የሚታወቅ ታላቅ ህዝብ ነው ብለዋል።
ከዚህ ህዝብ ጋር አብሮ መኖር ለጋራ እሴትና ልማት ላቅ ያለ ድርሻ አለው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ብሔረሰቡ የሚታወቅበትን ሀገር በቀል ግጭት አፈታት ዘዴንና ቋንቋቸውን በማልማት ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ዞኑ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የማጃንግ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ማንነትና ቱባ ባህል እንዳለው ያወሱት የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮናስ አበበ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘንግተው የቆየውን ባህልና እሴቶች ከወንድም ህዝቦች ጋር ለማልማት በመነሳታችን ታላቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
ባህላዊ ክዋኔዎችን ማልማት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመምከር ድርሻ አለው ያሉት አቶ ዮናስ: ለሀገር ዕድገት ብሎም ለዓለም- በተፈጥሮ ጥበቃ የራሱ አበርክቶ ያደረገው ህዝብ ማንነት እንዲለማ በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ይህ ታላቅ ኩነት ሁሉም ብሔርና ብሔረሰቦች በአንድነት በሚኖሩባት ቴፒ ከተማ በመከበሩ ደስታ ይሰማናል ያሉት ቱቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ገላቲያስ ሻሜ የማጃንግ ብሔረሰብ ቋንቋና ታሪክ በተፈለገው ደረጃ እንዲለማ የማስተባበሩን ስራ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በሲምፖዚየሙ በደቡብ ምዕራብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው እየቀረበ ይገኛል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚዘልቀው ሲምፖዚየም የብሔረሰቡን ማንነት የሚገልጹ የባህል ፌስቲቫል፣ የምግብና ቁሳቁስ አውደ-ርዕይ የሚካሄድ ሲሆን የብሔረሰቡ አዲስ ዘመን ማብሰሪያ ቀን እንደሚገለጽ ማወቅ ተችሏል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
