



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሸካ ዞን ማሻ ከተማ ህዝብ እንኳን ለሰው ልጅ ለተፈጥሮ ሀብት የሰጠው እንክብካቤ የሚደነቅ መሆኑን በጎበኙት ተፈጥሮ ሀብት ማረጋገጣቸውን 3ኛው ክልል ዓቀፍ የባህል ስፖርቶችና ባህል ፌስቲቫል ውድድር ልዑካን ቡድኖች ተናግረዋል።
3ኛው ክልል ዓቀፍ 21ኛው የባህል ስፖርቶችና 17ኛው ባህል ፌስቲቫል ተወዳዳሪ ልዑኳን ቡድኖች ከውድድሩ ጎን ለጎን በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የሚገኘውን የተለያዩ ተፈጥሮ ሀብቶችን ጎብኝተዋል።
በሸካ ዞን ካሉት በርካታ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች መካከል በማሻ ወረዳ የሚገኘውና ከማሻ ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ውብ ተፈጥሮና የተመልካችን ቀልብ የሚስብ የሸክሸኮ ፏፏቴና ዋሻ እንዲሁም የባሮ ወንዝ በልዑኳን ቡድኖች ከተጎበኙት መካከል ይገኛሉ ።
የማሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍን አዳሾ በጉብኝቱ ወቅት ልዑኳን ቡድኑን እንኳን በተፈጥሮ ወደ ታደለች ሸካ ዞን እንዲሁም ማሻ ወረዳ በሰላም መጣችሁ ብለዋል።
ወረዳችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች በመሆኑ ባያችሁትና በጎኛችሁት መሠረት ሌሎችም መጥተው እንድጎበኙ በማድረግ የጋራ ሀብታችንን በጋራ በመጠቀሙ በኩል ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
ልዑኳን ቡድኖች በወቅቱ በሰጡት አስተያየታቸው በአከባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በሚዲያ ከምንሰማው በላይ በአካል ተገኝተው ማየት በመቻላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
ተጠብቆ የቆዩ የአከባቢው እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን ማልማት፣መጠበቅና መንከባከብ ከዚህም ባሻገርም ለአለም ለማስተዋወቅ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል በአስተያየታቸው።
በጉብኙቱ ዳውሮ፣ኮንታ፣ምዕራብ ኦሞ፣ቤንች ሸኮ፣ ካፋና የሸካ ብሔረሰብ የባህል ስፖርቶችና ባህል ፌስቲቫል ውድድር ልዑኳን ቡድኖች ተሳትፎበታል።
በፍቅር ከበደ
