ግብርና ምርምር ለግብርናው ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዘርፈ-ብዙ ነዉ።

የግብርና ምርትና ምርታማነት ማነቆ መፍታት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ውጤታማነታቸው የተረጋገጡትን በማባዛትና በማላመድ ረገድ አይነተኛ ሚና ይጫወታል።
በዚህም የአከባቢን ሥነምህዳር ያገናዘቡ እምቅ አቅሞችን በመለየት ለግብርና ፖሊሲ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ መሠረታዊ ዳሳሳ ጥናት ማድረግና ለግብርና ተቋም ገንቢ ምክረ ሀሳብ የማቅረብ ሥራዎችንም ይሰራል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የተደገፉ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ፣ ማፍለቅ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን አባዝቶ ለምርጥ ዘር ድርጅትና ለተደራጁ አባዥ አካላት ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ኢንስቲትዩት በተጠናቀቀዉ በ2017 በጀት ዓመት በተፈጥሮ፣ በሰብል እና በእንስሳት ዘርፍ 70 በምርምር ምርታማነታቸው የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ማጠናቀቁን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ አስታውቀዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የግብርና ምርታማነት ማነቆ ሊፈቱ የሚችሉ ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣በማባዛትና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል።




በዚህም ለምርታማነት መጨመር አቅም የሚሆኑ ሰብሎችን በተለይም በሰብል አይነት አገዳ፣ብዕር ሰብሎች፣አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሥራሥር ሰብሎችን በማባዛት በአርሶ አደሩ ዘንድ እንዲላመድ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ዘርፎች በአከባቢ ያሉ ዘረመሎችን በመሰብሰብ በተለያዩ በዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማስገምገም ምርምር ውጤቶችን በማፍለቅ እና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡትን ወደአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ውጤቶች እንዲፈተሽ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል።
በሰብል ምርምር ዘርፍ የአከባቢው ፖቴንሽያል የሆነ የቡና ዝሪያ እንደክልል በመሰብሰብ በሀገራዊ ና ክልላዊ ዝሪያ ምርምር በቡናና በእንሰት ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
በእንስሳት ዘርፍ በተነዳፍ እና ተነዳፍ ባልሆኑ ንቦች፣በእንስሳት መኖ፣በዝሪያ ማሻሻያ በቦንጋ በግ ዝሪያ እና በዳውሮ በግ ዝሪያ እንድሁም በካፋ ፍየል ማሻሻያ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።
በአከባቢው ለግብርና ምርታማነት ማነቆ በሆነ የአፈር አሲዳማነት በኖራ ለማከም፣ በተፈጥሮ ማዳበሪያ (ቨርሚ ኮምፖስት) እንዲሁም በተቀናጄ የማዳበሪያ በመጠቀም የአፈር ለምነትን ለመመለስ እና ምርታማነት እንዲያድግ እየተደረገ ይገኛል ያሉት አቶ አማኑኤል በተለይ በሰዉ ሰራሽና ቨርሚ ኮምፖስት ሰፊ ትኩረት በማድረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ለሚያቋቁመው ማህበራት መነሻ ዘር በመሆን እያገለገለ ይገኛልም ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ባጠናቀቀዉ ዓመት 500 ኩንታል የሩዝ ምርት በክልሉ ግብርና ቢሮ በኩል ለሚያባዙ አካላት እንዲቀርብ እና ድንችና ስንዴ ለሚያባዙ አርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።




2017 በጀት ዓመት በምርምር ሥራዎች ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ እስካሁን ካሳለፍናቸው ዓመታት ተግባራትን በቅንጅት የተመራበት እና ምርታማነትን ለማረጋገጥ አርሶ አደሩን ባሳተፈ መልኩ ሥራዎች የተከናወኑበት ዓመት ነው ሲሉም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።
ምርምር በአንድ ጀምበር የሚያልቅ አይደለም ምርምር የሂደት ውጤት ነው ያሉት አቶ አማኑኤል በምርምር ክፍሎች በሰብል፣በተፈጥሮ እና በእንስሳት ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑንም በንግግራቸው ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩት በ2017 በጀት ዓመት በተፈጥሮ፣በሰብል እና በእንስሳት ዘርፍ የምርምር ውጤቶች የተጠናቀቁ ሲሆን ቴክኖሎጂዎችቹ በፓኬጅ ተዘጋጅተዉ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ ተዘጋጅቷሉም ነው ያሉት።
የምርምር ኢንስቲትዩት ሀብት በማፈላለግ ክልሉ ከሚመደበው ት ምርምር ማዕከላትን ማጠናከር፣መደገፍ፣የሚበጀተው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን መከታተል የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የግብርና ምርትና ምርታማነት ማረጋገጥ እና ለሚያጋጥሙ ማነቆዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዚህም የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በአራቱ ዞኖች ማለትም በካፋ፣ቤንች ሸኮ፣ሸካ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል በዳውሮና ኮንታ ዞኖች ለግብርና ምርታማነት አጋዥ የሆኑ የምርምር ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛልም ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ሀብት በመመደብ እና በሌሎች ድጋፎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ እጅግ የሚመሰገን ሲሆን መጠናከር እዳለበት የጠየቁት አቶ አማኑኤል አሁንም ለዘርፉ ሥራ መሳካት የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሟሉ አስፈላጋውን ድጋፍ እንዲደረግም አመልክቷል።
የግብርና ምርምር ተግባራት በቅንጅት የሚመራ ተግባር በመሆኑ በምርምር የወጡ ውጤቶች ወደ አርሶ አደሮች ተደራሽ በመሆን ውጤታማ እንዲሆኑ በማስተዋወቅና በማባዛት ረገድ በተለያዩ ደረጃ ያሉት የግብርና ዘርፍ እና አባዥ አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
