




በኢፌዴሪ የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የጅማ ድስትሪክት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል።
በምክክሩ መድረክ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደሩ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነቶችን በመፍጠር ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ጤናማ የስራ ግንኙነት እንዲፈጠርም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
በግል ድርጅቶች ያገለገሉ ሠራተኞች ለዘላቂ ዋስትና የሚሆናቸውን የጡረታ ዋስትና እንዲኖራቸውም ከማድረግ አንጻር በርካታ ስራዎችን መስራት መቻሉንም አቶ ተስፋዬ እንዳሻው ተናግረዋል ።
በኢፌዴሪ የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የጅማ ድስትሪክት በሶስት ክልሎች አራት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በመክፈት በ10 ዞኖች፣በ81 ወረዳዎች የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ በቀረበው ሰነድ ተብራርቷል ።
ዜጎች የጡረታ መብታቸውን የሚከበርበትን አሰራር በማሻሻል በአጭር ጊዜ መብታቸውን የሚያስከብሩበት ሁኔታ ድስትሪክቱ ማመቻቸቱም ተገልጿል ።
ድስትሪክቱ የጂማ ድስትሪክት የኋላ ታሪክ፣ የኦፕሬሽን ስራዎችና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በአቶ መስፍን መሸሻ፣ በአቶ መሠረት ዘለቀና በአቶ አባተ ምትኩ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በቀረቡት የመወያያ ሰነዶች ከባለድርሻ አካላት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ከተነሱ አስተያየቶችም ተገቢውን የጡረታ ዋስትና ገቢ ለመሰብሰብ በተቋማት በቂ የሰው ሀይልና በጀት አለመኖር ለስራው ስኬታማነት ማነቆ ይሆናል ይህ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተነስቷል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አንዳንድ መሠረታዊ ችግሮች ከተቃለሉ ስራውን በመተባበርና በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በክልሉ የዳውሮና ኮንታ ዞኖች ተጠሪነታቸው ለወላይታ ቅርንጫፍ መሆኑ ለአሰራር አመቺ አለመሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።
በውይይቱ በተነሱ አስተያየቶች እና የግንዛቤ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
መድረኩን ያጠቃለሉት የኢፌዴሪ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አባተ ምትኩ የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዓላማ ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
ለዚህም በክልሉ በግል ድርጅቶች ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞች ለነገ ዋስትናቸው የጡረታ ዋስትና ገቢ አሰባሰብ በቅንጅት ተባብረን በመስራት የረካ ጡረተኞችን መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል ።
በግል ድርጅቶች ዳውሮና የኮንታ ዞን አካባቢዎች ተጠሪነታቸው ከወላይታ ቅርንጫፍ ወደ ክልሉ ቅርንጫፍ የሚሆኑበት የአሰራር ጥናት እየተሰራም እንደሆነ አቶ አባተ ተናግረዋል ።
ለአሰራር አመቺ ያልሆኑ አንዳንድ ጉዳዮችን በመቀራረብና በመቀናጀት በመስራት ውጤታማ ለመሆን በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል ።
የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የጂማ ድስትሪክት በ3 ክልሎች 4 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በመክፈት 18,857 የግል ድርጅቶችንና 91,334 የግል ድርጅቶች ሠራተኞችን በመመዝገብ አባል አድርጎ እየሰራ ነው።
በታጠቅ አበበ
