




ከቴፒ ሺሽንዳ በመገንባት ላይ ያለው የአስፓልት መንገድ በመጓተቱ ለእንግልት ተዳርገናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞለት ግንባታው የተጀመረው 77 ኪ.ሜ የሚረዝመው የሺሺንዳ ቴፒ አስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ተቋርጦ መቅረቱ ለእንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን የቢጣ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የመንገድ ሥራው ስድስት ዓመታትን የፈጀ ቢሆንም ከቁፋሮ በዘለለ የተሻለ ክንውን እንደሌለው ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።
የመንገድ ግንባታው ተጀምሮ በመቋረጡ ያመረቱትን ወደ ገበያ ለማውጣት እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለመውሰድ ከባድ ፈተና እንደሆነባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የመንገዱ መበላሸት ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።
በመንገድ ግንባታ ሰበብ ቀደም ሲል ይገለገሉበት የነበረው መንገድም ከጥቅም ውጪ ሆኖብናልም ይላሉ።
በካፋ ዞን የቢጣ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ በቁፋሮ ሥራ ብቻ ቆሞ የቀረው መንገዱ ክረምት ሲመጣ ጎርፍና ናዳ የግለሰቦችን ቤትና ተቋማትን እያፈረሰ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር መነሻ ሆኗል ብሏል።
በቻይናው CRCC ድርጅት እየተገነባ ያለው የሺሽንዳ ቴፒ አስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ከተጀመረ 6 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም አፈጻጸሙ ገና 32% ብቻ መሆኑን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከፌደራል መንገዶች አስተዳደር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዝናባማ የአየር ጸባይ፣ የግንባታ ግብዓት ዋጋ መናርና የኮንትራክተሩ አቅም ማነስ ለመንገድ ፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያቶች መሆናቸውን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሚዛን አካባቢ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላዬ ንጋቱ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታትም ከሥራ ተቋራጩ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንና በቀጣይ ሁለት ዓመታት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል ሲል ኤፍ ኤም ሲ ሚዛን ቅርንጫፍ ዘግቧል።
