የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን የካቲት 5 እና 6 እንደሚያካሄድ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ገልፀዋል።

Spread the love

የ2018 ዓ.ም ግማሽ ዓመት የአስፈፃሚ አካላት ስራ ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎች በጉባኤው እንደሚቀርቡም አመላክተዋል።

ከጉባኤው አስቀድሞ ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴና በጽ/ቤት አማካኝነት በግማሽ ዓመት ለማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት መካከል በተለይም የድጋፍና ክትትል እንዲሁም የቁጥጥር ስራዎችን በ5ቱም ዘርፍ ሰርቶ ማጠናቀቁን የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አሳውቀዋል።

በተጨማሪ የቋሚ ኮሚቴ ስራ ሪፖርት ተገምግሞ ግብረ መልስ ተሰጥቷል ብለዋል።

ከግምገማው በኋላ እንደ ክልል የተያዙ ካፒታል ኘሮጀክቶችን በሚመለከት በተለይ የውሃ፣የመንገድና የመስኖ አውታሮችን ጨምሮ በርካታ መሠረተ-ልማቶች እየተመረቁ ያሉበት ሂደት መኖሩን ጠቁመው ቀሪ ኘሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የካቲት 4 የተከበሩ የምክር ቤት አባላት፣አስፈፃሚ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ጉባኤውን ለመታደም የምክር ቤቱ መቀመጫ ወደሆነችው ታርጫ ከተማ የሚገቡ ይሆናል።

በመጨረሻም እንግዶች ወደ ብዝሃ ማዕከሏ ታርጫ ሲመጡ የከተማዋ ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ አቀባበል እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *