ተስፋ ሰጪው ኢንዱስትሪ

Spread the love

ተስፋ ሰጪው ኢንዱስትሪ

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከሚያስተዳድራቸው ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዉስጥ የሚገኝ ነው ፡፡

ፋብሪካው በ2008 ዓ/ም የተቋቋመ ሲሆን ከፋብሪካ ግንባታ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 እና ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ ገብረየስ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ተቋቁሞ ወደ ተግባር ከገባ ወዲህ በ4 የተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገንም አቶ ጥበቡ ተናግረዋል ፡፡

በዚህም ፋብሪካው በእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ የሸንኮራ አገዳና ሌሎች ሰብሎች ላይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚመራ ዘርፍ እንደሆነም ገልጸዋል ፡፡

አሁን ላይ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ካላው 25 ሺህ ሄክታር መሬት 5 ሺህ 400 ሄክታር በሸንኮራ አገዳ ልማት መሸፈኑንና 6 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎና ሌሎች ሰብሎች መልማቱን በመግለጽ ቀሪ መሬት በሌሎች ሰብሎች ለመሸፈን የመሬት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል ፡፡

ፋብሪካው የኦፕሬሽን ዘርፍ ሌላይኛው የፋብሪካው ዘርፍ ሲሆን በዚህ ዘርፍ የሸንኮራ አገዳ በመከትከትና ፕሮሰስ በማድረግ ወደ ስኳርና ለሌሎች ስራዎች የሚቀይር መሆኑንም አብራርተዋል ፡፡

በ3ኛ ደረጃ ፋብሪካው ትኩረት አድርጎ የሚሰራበት ዘርፍ የሰው ሀብትና የአቅርቦት ዘርፍ ሲሆን የፋብሪካውን ሰው ሀይል በማደራጀትና በማሰልጠን ለስራ ብቁ እንዲሆኑ በማድረግም በስፋት እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ጥበቡ አስረድተዋል ፡፡

በ4ኛ ደረጃ የተመለከተው ዘርፍ ዋና ስራ አስኪጅ ጽ/ቤት ዘርፍ ሲሆን ይህም ተለያዩ አደረጃጀቶችን በመዘርጋት ፋብሪካው ውጤታማ ስራዎችን እንዲሰራ ለማስቻል ተደርጎ መዋቀሩን አብራርተዋል ፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ አሁን ላይ ሸንኮራ አገዳ የማልማቱን ስራ እያከናወነ የሚገኘው ከሻርማ ወንዝ በተጠለፈ የመስኖ አውታር እንደሆነም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል ፡፡

በቆላማና መስኖ ሚኒስቴር አማካኝነት በኦሞ ወንዝ ላይ ተጠልፎ እየተገነባ የሚገኘው የኮፈር ግድብ ሲጠናቀቅ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 እና ቁጥር 5 ስኳር ፋብሪካዎች የማልማት አቅማቸውን በእጅጉ የሚያሳድግ ስለመሆኑም አቶ ጥበቡ አስረድተዋል ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ በይዞታው የለማውን 5400 ሄክታር የሸንኮራ አገዳና ከኦሞ ኩራዝ 1 ስኳር ፋብሪካ የለማውን 7 ሺህ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ በጥቅሉ 12 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ የለማውን የሸንኮራ አገዳ በመጠቀም ስኳር እያመረተ እንደሚገኝም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል ፡፡

ፋብሪካው በዓመት በሁለት ዙር 245 ሺህ ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅዶ እየሰራ ሲሆን በቀጣይ ሰኔ ወር ጀምሮ የዓመቱን ምርት ለማጠናቀቅ እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ጥበቡ ተናግረዋል ፡፡

ፋብሪካው በዋናነት ስኳር ያምርት እንጂ በተጓዳኝ በተረፈ ምርቶች ሞላሰስ፣ የባጋስ ምርት እና ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛልም ፡፡ ከፋብሪካው የሚገኘው ባጋስ/ገለባ ተረፈ ምርት/ በፋብሪካው ውስጥ ባሉት 2 ቦይለሮች በእያንዳንዳቸው 30 ሜጋ ዋት በድምሩ 60 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ በማመንጨት ከዚህም ውስጥ 13 ሜጋ ዋት ያህሉን ብቻ ፋብሪካው እየተጠቀመ እንደሚገኝና ትርፍ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ለመሸጥም በዕቅድ ላይ እንደሚገኙም አቶ ሙመድ የፋብሪካው ኦፕሬሽን ምክትል ስራአስኪያጅ በጉብኝት ወቅት አስረድተዋል ፡፡

ለዜጎች ስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በፋብሪካው በቋሚነት 1920 ፣ በጊዜያዊነት 2600 የሰው ሀይል እነደሚገን ስራአስኪያጅ ጥበቡ አስረድተዋል ፡፡ ለፋብሪካው ግብኣት የሸንኮራ አገዳ ምርት ለቆረጣ በሚደርስበት ወቅት ደግሞ እስከ 6000 ለሚደርሱ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል እየተፈጠረላቸው እንደሚገኝም የአቶ ጥበቡ ገለጻ ያስረዳል ፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣በ4 ሳይቶች የጤና ተቋማትን በመክፈት የህክምና አገልግሎቶችን በነጻ መስጠት፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን አንድ ደረጃውን የጠበቀ ከ1-8ኛ ክፍል የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባትና ቁሳቁሶችን በማሟላት በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የሚጠበቅበትን ማህበራዊ መስተጋብር እየተወጣ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ፋብሪካው በዓመት 120 ሺህ ኩንታል ለማምረት እንዲያስችለው ተደርጎ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቴክኖሎጂን ታግዞ የተቋቋመ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችለውን ስራዎች እየሰራ የሚገኝ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የጸጥታ ስጋቶች ለስራው አደናቃፊ እንዳይሆኑ እንዲቀረፉም አቶ ጥበቡ ጠይቀዋል ፡፡

በመጨረሻም አቶ ጥበቡ ፋብሪካው የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በሚገባ ለመወጣት እንዲያስችለው የክልሉ መንግስት የጀመረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ስራዎችን አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጠይቀዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *